የዩናይትድ ኪንግደም ቤተ-መንግሥት ከቀረበበት ወቀሳ በኋላ ‘የብዝሃነት’ ፖሊሲዬን እየመረመርኩ ነው አለ

ንግስት ኤሊዛቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ንግስት ኤሊዛቤት

የንግስት ኤሊዛቤት ይፋዊ መኖሪያ የሆነው ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት በንጉሳውያን መኖሪያዎች ውስጥ የብዝሃነት ፖሊሲዎችን እየመረመርኩ ነው አለ።

ይህ ምርመራ የሚካሄደው የንጉሳዊያኑ ቤተሰብ መኖሪያ በሆኑት በባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት፣ ክሌሬንስ ሃውስ እና ኪንግስተን ቤተ-መንግሥቶች ውስጥ ብዝሃነትን ለማሻሻል ነው ተብሏል።

ምንጮች እንደሚሉት ቤተ-መንግሥቱ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ብዝሃነትን ለማስፋት ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች እና ፕሮግራሞች ቢኖሩትም በሚፈለገው መጠን ለውጥ አልመጣም።

ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት የብዝሃነት ፖሊሲዬን ላጤን ነው ያለው፤ ልዑል ሃሪ እና ባለቤቱ ሜጋን በቤተ-መንግሥቱ ውስጥ ዘረኝነት አለ የሚል ቅሬታ ካሰሙ በኋላ ነው።

ልዑል ሃሪ እና ከጥቁር እናት የተገኘችው ባለቤቱ ሜጋን ከኦፕራ ዊንፍሬይ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የተረገዘው ልጅ ሲወለድ የቆዳ ቀለሙ ምን ያክል ጥቁር ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ቀርቦላቸው እንደነበረ ተናግረዋል።

ጥንዶቹ ይህን እስተያየት ማን እንደሰጠ ያሉት ነገር ባይኖርም ልዑል ሃሪ ግን ንግስት ኤሊዛቤት ወይም የንግስቷ ባለቤት ልዑል ፊሊፕ ይህን አስተያየት አለመስጠታቸውን ለኦፕራ አረጋግጧል።

የጥንዶቹ ቃል-መጠይቅ ለንጉሳዊያኑ ቤተሰብ አስቸጋሪ ሁኔታን የፈጠረ ነበር ተብሏል።

ለዚህም ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ጉዳዩን በአጽንኦት ተመልክቶ እና ‘ቤተሰቡ በግል መፍትሄ ይሰጥበታል’ ብሎ ነበር።

ይህ የብዛህነት ምርምራ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ማህበረሰብ አባላት፣ አካል ጉዳተኞች እና የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን የቤተ-መንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ይጥራል ተብሏል።

የብዝሃነት ጉዳይንም ለመመርመር ቤተ-መንግሥቱ ገለልተኛ የሆነ አካል አመለካከትን የምርመራው አካል ለማደረግ ቁርጠኛ ነውም ተብሏል።

ይህ የብዝሃነት ምርመራ “የብዝሃነት አለቃ” የሚል ማዕረግ ያለው ግለሰብ ቅጥርንም ሊያስተዋውቅ እንደሚችል ተጠቁሟል።