ልዑል ሃሪና ሜጋን ከዚህ በኋላ የገቢ ምንጫቸው ምን ይሆናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ልዑል ሃሪ ንጉሣዊው ቤተሰቡ ለሱና ለባለቤቱ ይሰጡትን የነበረውን የገንዘብ ድጎማ ማቋረጣቸውን ይፋ አድርጓል።
ይህ የሆነው ልዑሉና ባለቤቱ ሜጋን ከነባር የንጉሣዊያን ቤተሰብ አባልነት 'ራሳቸውን አግልለው' ወደ ካሊፎርኒያ በማቅናታቸው ነው።
እና አሁን የገቢ ምንጫቸው ምን ይሆናል? ልዑል ሃሪና ሜጋን ከንጉሣዊው ቤሰተብ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ ይኖር ይሆን?
የሰሴክስ ዱክና ደችስ በመባል የሚታወቁት ሜጋንና ሃሪ ባለፈው ዓመት ጥር ነበር የንጉሣዊ ቤተሰብ አባልነት በቃን ብለው የወሰኑት።
በወቅቱ ራሳቸውን በገንዘብ ለመቻል ቃል ገብተውም ነበር።
ነገር ግን በጊዜው ጥንዶቹ በገቡት ስምምነት መሠረት ከሃሪ አባት የገንዘብ ድጎማ ይደረግላቸው እንደነበር ይነገራል።
የሃሪ አባት የሆኑት ልዑል ቻርልስ የሒሳብ መዝገብ እንደሚያሳየው ሃሪና ሜጋንን ጨምሮ የካምብሪጅ ዱክና ደችስ ተብለው ለሚታወቁት ጥንዶች የሚሆን 5.6 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጓል።
ይህ ወጪ እስከ መጋቢት 2020 ያለውን ጊዜ የሚያሳይ ነው።
ነገር ግን ልዑል ሃሪ ከዚህ ወቅት ጀምሮ የገንዘብ ድጎማ ተቋርጦብኛል ሲል ለጉምቱዋ አሜሪካዊት ቃለ-ምልልስ አድርራጊ ኦፕራ ዊንፍሬይ ነግሯታል።
ቢሆንም ልዑሉ እያወራ ያለው ከአባቱ ኪስ ስለሚሰጠው ገንዘብ ይሁን አሊያም ከግብር ከፋዩ ማሕበረሰብ ወይም ከሁለቱ ግልፅ አይደለም።
ከመጋቢት ጀምሮ ያለው የልዑል ቻርልስ ሒሳብ ዝርዝር መረጃ ይፋ አልደተረገም። ቤተ-መንግሥቱም በዚህ ጉዳይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሃሪና ሜጋን ሃብታም ናቸው?
የሰሴክስ ዱክና ደችስ በመባል የሚታወቁት ሃሪን ሜጋን የማይናቅ ሃብት አላቸው።
ልዑል ዊሊያምና ልዑል ሃሪ በድምሩ 13 ሚሊዮን ዩሮ ከእናታቸው ልዕልት ዳያና ወርሰዋል።
ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አሜሪካ እንደመጡ ለኦፕራ የነገራት ሃሪ "እናቴ ትታልኝ የሄደችው ነገር ባይኖር ኖሮ ይሄን ማድረግ አንችልም ነበር" ብሏል።
የቢቢሲው የንጉሣዊያን ቤተሰብ ተንታኝ ኒክ ዊቼል ደግሞ ልዑል ሃሪ ከአያቱ [ንግሥት ኤሊዛቤት] ሚሊዮን ፓውንዶች ወርሷል ይላል።
በሌላ በኩል ሜጋን ተዋናይት በነበረችበት ወቅት ሱትስ በተሰኘው ተከታታይ ድራማ ላይ ስትተውን በአንድ ክፍል 50 ሺህ ዶላር ይከፈላት እንደነበር ይነገራል።
ሜጋን ከዚህ በተጨማሪ 'የላይፍስታይል' መጦመሪያ [ብሎግ] እና ለአንድ የካናዳ ልብስ አምራች የሚሸጥ የፋሽን ዲዛይን አላት።
ሌላ የገቢ ምንጫቸው ምንድነው?
አሁን ጥንዶቹ ከንጉሣዊው ቤተሰብ ጋር ያላቸው ውል ስለተቀደደ ያሻቸውን ነገር መሥራት ይችላሉ።
ጥንዶቹ ከኦፕራ ጋር ያደረጉት ቆይታ በክፍያ አልነበረም። ነገር ግን ኔትፍሊክስና ስፖቲፋይ ከተሰኙት ድርጅቶች ጋር ውል ገብተዋል። እነዚህ ስምምነቶች በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚያስገቡላቸው ይታመናል።
ሜጋንና ሃሪ አርችዌል የተሰኘ ተቋም አላቸው። ይህ ድርጅት ከአንድ ሌላ የእርዳታ ድርጅት ጋር ይሠራል።
ጥንዶቹ ዩናይትድ ኪንግደም እያሉ ጥበቃ ይመድብላቸው ነበር። የጥበቃው ሒሳብ ምን ያክል እንደሆነ አይታወቅም።
የካናዳ መንግሥት ለጥንዶቹ የሚያደርገውን ጥበቃ እንደሚያቆም ሲያሳውቅ ነው ሜጋንና ሃሪ ወደ አሜሪካ ያቀኑት።
ይሄኔ አሜሪካዊው ቢሊየነር ታይለር ፔሪ እስኪደላደሉ ድረስ መኖሪያ ቤትና ጥበቃ እንዳበረከተላቸው ጥንዶቹ ተናግረዋል።
"ለኔ ዋናው ነገር የቤተሰቤን ደህንነት ለመጠበቅ በቂ የሆነ ገንዘብ ማግኘት ነበር" ሲል ሃሪ ለኦፕራ ነግሯታል።
ጥንዶቹ የንጉሣዊው ቤተሰብ ኃላፊነት ይብቃን ከማለታቸው በፊት 95 በመቶ የገቢያቸው ምንጭ የሃሪ አባት ልዑል ቻርልስ ነበሩ።
ለምሳሌ በፈረንጆቹ 2018-19 ብቻ ለሜጋንና ሃሪ እንዲሁም ለካምብሪጅ ዱክና ደችስ ከ25 ሚሊዮን በላይ ዩሮ ፈሰስ ተደርጓል።
ከግብር ከፋዩ የሚገኘው ገቢ ደግሞ 5 በመቶ የሚሆነው ወጪ ይሸንፋል።
ጥንዶቹ ከቤተሰቡ በወጡ ጊዜ በታክስ ከፋዩ ገንዘብ አሳደሱት የተባለውን ቤት ወጪ 2.4 ሚሊዮን ዩሮ መመለሳቸው አይዘነጋም።












