የልዕልት ዲያና ደብዳቤዎች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው

የልዕልት ዲያና ደብዳቤዎች

የፎቶው ባለመብት, David Lay Auctions

የዌልስ ልዕልት በነበረችው ዲያና በእጅ የተፃፉ ደብዳቤዎች ከሰሞኑ በእንግሊዙ ለጨረታ ሊቀርቡ ነው።

የጨረታ አቅራቢው ኮርንዋል እንዳስታወቀው አርባ ደብዳቤዎችንና የሰላምታ ካርዶችንም አዘጋጅቷል።

ደብዳቤዎቹ በአውሮፓውያኑ 1990-1997 የተፃፉ ሲሆኑ፤ ለጓደኛዋ ሮጀር ብራምብል የተፃፉ ደብዳቤዎች ተካትተውበታል ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 12 1992 ተፃፈ በተባለ ደብደቤ "አስፈሪ ሳምንት" ነው ስትል ገልፃ ነበር።

በወቅቱም አንድሪው ሞርተን የተባለ ጋዜጠኛ የልዕልቲቱን ህይወት ታሪክ ያሳተመበት ወቅት ሲሆን የመፅሃፉ ታሪክም በሰንደይ ታይምስ እየተቀነጨበ እየቀረበ ነበር።

ደብዳቤዎቹ ከ300 ፓውንድ-1500 ፓውንድ ዋጋ ተተምኖላቸዋል።

የልዕልት ዲያና ደብዳቤዎች

የፎቶው ባለመብት, David Lay Auction

ዴቪድ ሌይ የተባለ የጨረታ አቅራቢ ሰራተኛ የሆነችው ኮኔል ሌይ እንደምትለው "የልዕልቲቷን ደብዳቤ ላየ በፍቅር የተሞላች፣ አስቂኝ፣ ቀልደኛ፣ ደግ፣ ልበ ሩህሩህና ማራኪ መሆኗን መገንዘብ ይቻላል። ለዚያም ነው ደብዳቤዎቹን በጨረታ ለማቅረብ የተዘጋጀነው"

በአንደኛው ደብዳቤ ላይ የምሳ ግብዣን ውድቅ ታደርግና የፈገግታ ስዕልም ጨምራበታለች።

"ከተለያዩ አገራት የዲያናን ደብዳቤ መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች እየጠየቁን ነው ያሉት። በተለይም ከአሜሪካ በርካቶች ናቸው ደብዳቤዎቹን የመግዛት ፍላጎት ያሳዩት፤ ከዚህ በተጨማሪ ከህንድም እንዲሁ እየጠየቁን ነው" ትላለች።

የደብዳቤዎቹ ሽያጭ ከልዕልቲቷና ከጓደኛዋ ሮጀር ብራምብል ስም ጋር ግንኙነት አላቸው ለሚባሉ ድርጅቶች ይውላል ተብሏል።

ከነዚህም መካከል የእንግሊዙ ብሄራዊ ባሌትና ያንግ ሚዩዚሻንስ ሲምፎኒ ኦርኬስትራ ተቋማት ይገኙበታል።

ጨረታው ከሳምንት በኋላ ክፍት እንደሚሆንም ተዘግቧል።