ቻይናና ሩሲያ በጨረቃ ላይ የጠፈር ጣቢያ ለመገንባት ተስማሙ

የጨረቃ ምስል

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ቻይናና ሩሲያ በጨረቃ ላይ የጠፈር ጣቢያ ለመገንባት ተስማምተዋል።

የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ሮስኮሞስ እንዳስታወቀው ከቻይና ብሔራዊ የጠፈር አስተዳደር ጋር በጨረቃ ላይ፣ ወይም በዛቢያዋ ላይ የምርምር ማዕከል ለመገንባት ከስምምነት ላይ መደረሱን ነው።

ይህንንም ሁለቱ ሃገራት በፊርማ ማፅደቃቸውን ነው።

ከሁለቱም ሃገራት የጠፈር ኤጀንሲ የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ከግንባታው በኋላ ሁለቱ ሃገራት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ነው።

ይኼ ዜና የወጣው ሩሲያ በጠፈር ላይ ያደረገችውን የመጀመሪያ በረራ 60ኛ አመት መታሰቢያ ክብረ በዓል በምታከብርበት ወቅት ነው።

በጨረቃ ላይ የሚገነባው አለም አቀፉ የሳይንስ የጠፈር ጣቢያ በርካታ ሳይንሳዊ ምርምሮች ይካሄዱበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከነዚህም መካከል ጨረቃን መጠቀም የሚቻልበትን መንገዶች ያካተተም እንደሆነ ከሁለቱ አገራት ኤጀንሲዎች የወጡ መግለጫዎች ያሳያሉ።

"ቻይናና ሩሲያ በጠፈር ሳይንስ፣ ምርምርና ልማት ላይ እንዲሁም በጠፈር ላይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ የተከማቸ ጥምር ልምዳቸውን በመጠቀም በጨረቃ ላይ አለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያን ለመገንባት ተስማምተዋል" በማለትም ከቻይና በማንዳሪን ቋንቋ የወጣው መግለጫ አትቷል።

መግለጫው አክሎም ሁለቱ አገራት የምርምር ጣቢያውን በማቀድ፣ዲዛይን በማድረግ፣ በልማት እንዲሁም በቀን ተቀን ስራው ላይ እንደሚሳተፉ ይፋ አድርጓል።

በቻይና የጠፈር ፕሮግራም ላይ ተንታኝ የሆኑት ቼን ሌን ይህ ፕሮጀክት ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

"ለቻይና ይህ ፕሮጀክት በአለም አቀፉ የጠፈር ትብብር ትልቁ ነው፤ ስለዚህ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው" ብለዋል።

በጠፈር አሰሳ ላይ ዘግየት ብላ የተቀላቀለችው ቻይና በታህሳስ ወር ላይ ከጨረቃ ላይ ድንጋይና አፈር ማምጣት መቻሏን አስታውቃለች።

በወቅቱም ቻይና በጠፈር ላይ የምታደርገው ምርምር የላቀ ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳየ ነው ተብሏል።

በጠፈር አሰሳ ላይ የቀደምት ስፍራ የሚሰጣት ሩሲያ በበኩሏ በቅርቡ አሜሪካና ቻይና በሚያደርጉት እሽቅድምድም ወደኋላ ቀርታለች ተብሏል።