ወደ ጠፈር በመሄድ የመጀመሪያው ይሆን የነበረው አፍሪካዊ በሞተር አደጋ ሞተ

ማንዳላ ማሶኮ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማንዳላ ማሶኮ

ወደ ጠፈር ለመሄድ እድል አግኝቶ የነበረው ደቡብ አፍሪካዊ በሞተር አደጋ ሕይወቱ አለፈ።

ደቡብ አፍሪካዊው ማንደላ ማሶኮ ወደ ጠፈር የመሄድ ምኞቱ ቢሳካ ኖሮ ወደ ጠፈር የተጓዘው የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ይሆን ነበር።

የ30 ዓመቱ ወጣት ማንዳላ ማሶኮ ቅዳሜ ዕለት በሞተር አደጋ ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ አየር ኃይል አባል የነበረው ማንዳላ እአአ 2013 ላይ ወደ አሜሪካ ጠፈር አካዳሚ ለመግባት ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች ጋር ተወዳድሮ ከተመረጡ 23 ሰዎች መካከል አንዱ ለመሆን ችሎ ነበር።

ስፔስቦይ (የጠፈር ልጅ) እየተባለ በጓደኞቹ የሚጠራው ማንዳላ ማሶኮ፤ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት በሚገኘው የኬኔዲ ጠፈር ማዕከል ውስጥ ወደ ጠፈር የሚደረግ በረራ ልምምድ አድርጓል።

ማሶኮ "አፍሪካውያን ወጣቶችን ሊያነቃቃ የሚችል ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ከየትም ይምጡ ማሳካት የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ" ይል ነበር።

ማሶኮ ለቢቢሲ 'ከጠፈር ሆኘ እደውልላችኋለሁ" ሲል ተናግሯል። ''በቀጣዮቹ ዓመት ወደ ጠፈር ስሄድ የስልክ መስመር ይኖረኛል- ኒል አርምስትሮንግ እንደነበረው'' ብሎ ነበር።

ኒል አርምስትሮንግ አሜሪካዊ ጠፈርተኛ ሲሆን በ82 ዓመቱ እአአ 2012 ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። አርምስትሮንግ እአአ 1969 ላይ በጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተራመደ ሰው ነበር።

በጨረቃ ላይ የመጀመሪያ እርምጃውን እንዳደረገ ''ይህ ለአንድ ሰው ኢምንት እርምጃ ነው፤ ለሰው ልጆች ግን ግዙፍ ከፍታ ነው'' ሲል ተናግሮ ነበር።