"ደም የመሠለች ጨረቃ" ዛሬ ምሽት በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ ትታያለች

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ረዥሙ የጨረቃ ግርዶሽ

የፎቶው ባለመብት, NASA

ለአንድ ሰዓት ከ 43 ደቂቃ የሚዘልቀው ግርዶሽ ዛሬ ሐምሌ 20፣ 2010 ዓ. ም ይታያል። በ21ኛ ክፍለ ዘመን ለዚህን ያህል ጊዜ የቆየ ግርዶሽ አልታየም፣ አይታይምም።

የጨረቃ ግርዶሽ ምንድነው?

የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው መሬት፣ ጨረቃና ፀሐይ በሚያደርጉት መስተጋብር ነው። ፀሐይ፣ ምድርና ጨረቃና በሰልፍ ሲሰደሩ ግርዶሽ ይከሰታል። ይህም ማለት መሬት በፀሐይና በጨረቃ መሐል ድንገት ስትደነቀር ነው። በዚህን ጊዜ ወደ ጨረቃ የሚሄደው የፀሐይ ብርሃን በምድር ይጋረዳል።

ምድር በፀሐይና ጨረቃ መሐል መደንቀር ደግሞ አንዳች ጥላ ይፈጥራል። በዚህን ጊዜ ጨረቃ በተፈጠረው ጥላ መሐል ሰተት ብላ ስትዘልቅ የጨረቃ ግርዶሽ ተፈጠረ እንላለን።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን ረዥሙ የጨረቃ ግርዶሽ

ግርዶሹ የት ይታያል?

ግርዶሹን በጉልህ ማየት የሚቻለው በከፊል አውሮፓ፣ እሲያ፣ አፍሪካ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ አካባቢ ነው።

ከሰሜን አሜሪካ በስተቀር በአመዛኙ በተቀሩት አሕጉራት መታየት ይችላል።

ቀይዋን ጨረቃ ለማየት ቴሌስኮፕ አያስፈልግም። ቀለል ያለ አቅርቦ ማሳያ (ባይናኩላር) በቂ ነው።

በኢትዯጵያና አካባቢው ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ20 አካባቢ ማየት ይቻላል።

ቀይዋ ጨረቃ ከትርክና አካባቢው ስትታይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሚፈጠረው ግርጃ ጨረቃ ቀላ ያለ መልክ እንድትይዝ ያደርጋታል

የዛሬ ምሽቷ ጨረቃ ለምን ትቀላለች?

የጨረቃ ምህዋር ዘመም ያለ በመሆኑ ጨረቃ በየወሩ በምድር ጥላ በኩል ልታልፍ አትችልም። ለምን?

ከፀሐይ ብርሃን የሚመጣው የቀለማት ሽብልቅ በምድር ከባቢ አየር አማካይነት ይበተናል። ኾኖም ባለቀይ ቀለሙ ረዥም የጨረር ሞገድ ከባቢውን አልፎ በመግባት ወደ ጨረቃ ነጥሮ ይመለሳል። ይህ ኩነት ለጨረሩ የተለየ ደማቅ ቀይ ቀለም ይሰጠዋል።

ክስተቱ "የደም ጨረቃ" ወይም ቀይዋ ጨረቃ ተብሎ የሚጠራውም ለዚሁ ነው።

በጉልህ የሚታየው ከየት አካባቢ ነው?

ይህን ታሪካዊ ኩነት ለመታደም ሁነኛው ሥፍራ ምሥራቅ አፍሪካና መካከለኛው ኢሲያ ነው።

ኾኖም በመካከለኛውና በሰሜን አሜሪካ ግርዶሹን ለመመልከት አይቻልም።

ከምሥራቅ አፍሪካ ሌላ በደቡብ አሜሪካ በምሥራቁ ክፍል በተለይም በቦነስ አይረስ፣ ሳኦፖሎና ሪዯ ዲጂኔሩ የተሻለ ትታያለች።