ጨረቃን የሚረግጠው የመጀመሪያው ጎብኚ ታወቀ

የመጀመሪያው የጨረቃ ጎብኚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቢሊየነሩ ስምነት የሚሆኑ አርቲስቶች አብረውት እንዲጓዙ ይጋብዛል

ስፔስ ኤክስ የተሰኘው ኩባንያ ቱሪስት ሆኖ በመጀመሪያ ወደ ጨረቃ የሚሄደው ደንበኛው የ42 ዓመቱ ጃፓናዊ ቢሊየነር ያሱካ ማዚዋ እንደሆነ አስታወቀ።

ያሱካ ማዚዋም "ወደ ጨረቃ መሄድን መርጫለሁ"ብሏል።

ጨረቃን የሚጎበኘው ይህ ጃፓናዊ ቱሪስት ወደ ጨረቃ የሚመጥቀው ኩባያው እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 ይፋ ባደረገ መርሃግብር መሰረት መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የጨረቃ ጉዞ የታቀደው ለ2023 ሲሆን የናሳዋ አፖሎ 17 እንደ አውሮፓውያኑ በ1972 ጨረቃ ላይ ካረፈች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጅ ጨረቃን የሚረግጥበት አጋጣሚ ይሆናል ተብሏል።

ይህ ጉዞ ይፋ የተደረገው ዛሬ ኒዮርክ ላይ ሲሆን ኩባንያው "ወደ ህዋ የመጓዝ ህልም ላላቸው በየእለቱ መሄድ እንዲችሉ ለማድረግ ይህ ወሳኝ እርምጃ ነው" ብሏል።

ሚስተር ማዚዋ ባለፈው ዓመት ኒውዮርክ ላይ ተደርጎ በነበረ ጨረታ ለአንድ የስዕል ሥራ 110.5 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉን ተከትሎ የመገናኛ ብዙሃን ርዕስ ሆኖ ነበር።

ቢሊየነሩ ወደ ህዋ በሚያደርገው ጎዞ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ስድስት ወይም ስምንት አርቲስቶች አብረውት እንዲጓዙ እንደሚጋብዝም አስታውቋል።

"ወደ መሬት ሲመለሱ የሆነ ነገር እንዲሰሩ ይጠየቃሉ። እነዚህ የሚሰሩ ምርጥ የጥበብ ውጤቶች ለሁላችን መነሳሳትን ይፈጥራሉ" በማለት ቢሊየነሩ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።