ትራምፕ፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት 'በራሳቸው የማሕበር ሚድያ ገፅ' ሊመለሱ እንደሆነ ፍንጭ ሰጡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በራሳቸው የማሕበራዊ ሚዲያ አማካይነት ወደ ማሕበራዊ ሚድያ ሊመለሱ መሆኑን አማካሪያቸው ተናገሩ።

"ፕሬዝደንት ትራምፕ በሁለት በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ማሕበራዊ ሚድያ ተመልሰው እንደምናያቸው አስባለሁ" ሲሉ ጄሰን ሚለር ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።

አማካሪው እንደሚሉት ዶናልድ ትራምፕ የሚመለሱበት ማሕበራዊ ገፅ "በገበያው በጣም ተፈላጊው" ይሆናል።

አልፎም አዲሱ ማሕበራዊ ሚድያ "ጨዋታውን ይቀይራል" ይላሉ አማካሪው።

ባለፈው ጥር ካፒቶል በተሰኘው የአሜሪካ ሹማምንት መቀመጫ ላይ ከደረሰው ጥቃት በኋላ ትራምፕ ከፌስቡክና ከትዊተር መታገዳቸው ይታወሳል።

የትራምፕ ደጋፊዎች ባደረሱት በዚህ ጥቃት አንድ የፖሊስ መኮንን እንዲሁም ሌሎች አራት ሰዎች ተገድለዋል።

ጥቃቱ የአሜሪካን ዴሞክራሲ መሠረት ያነቀነቀ ተብሎለትም ነበር።

ይህ ጥቃት ከደረሰ ከቀናት በኋላ ትዊተር ከ87 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያፈራውን የትራምፕ ገፅ "ሌሎች ጥቃቶች ሊያነሳሳ ስለሚችል እስከመጨረሻው ተዘግቷል" ሲል አግዶታል።

ትራምፕ ትዊተርን ላለፉት 10 ዓመታት ደጋፊዎቻቸውን ከባሕላዊው መንገድ በተለየ መልኩ ለመድረስ ተጠቅመውበታል።

ወደ ገፁ አምርተው ያሻቸውን ይናገራሉ፤ የፈለጉትን ባለሥልጣን ይወርፋሉ፤ ደጋፊዎቻቸውን ያነሳሳሉ።

የትራምፕ አዲሱ ማሕበራዊ ድር ይታወቃል?

አይታወቅም።

አማካሪው ትራምፕ ለመጠቀም ስላሰቡት አዲሱ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረክ ምንም ዓይነት ማብራሪያ አልሰጡም።

"ሁሉም ሰው ፕሬዝደንት ትራምፕ ቀጣይ ምን እንደሚያደርጉ በጉገት ይጠብቃል፤ ይመለከታል" ብለዋል።

አማካሪው ለቴሌቪዠን ጣቢያው እንደተናገሩት ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው ማራላጎ በተሰኘው ልጥጡ ሪዞርታቸው ውስጥ ወሳኝ ከሚባሉ ሰዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።

"በርካታ ኩባንያዎች" የቀድሞውን ፕሬዝደንት ቀርበው እንዳናገሯቸው ነው አማካሪው የሚናገሩት።

ትራምፕ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞች ማምጣት ይችላሉ ብለው የሚያስቡት አማካሪው አዲሱ የማሕበራዊ ሚዲያ መድረክ የሚደርሰው የለም ባይ ናቸው።

ትራምፕ ወደ ካፒቶል ሄደው ሃገር ያርበደበዱትን ሰዎች "አርበኞች" ብለው መጥራታቸውን ያየው ትዊተር መጀመሪያ ለ12 ሰዓታት ከገፁ አግዷቸው ነበር።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የትራምፕ ደጋፊዎች ወደ ካፒቶል ያመሩት የአሜሪካ ኮንግረስ ጆ ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ለማወጅ ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት ነበር።

ትዊተር 'ከዚህ በኋላ ሕግ የሚጥሱ ከሆነ ወየልዎ' ሲል የቀድሞውን ፕሬዝደንት አስጠነቀቀ።

ወደ ገፃቸው እንደሚለሱ የተፈቀደላቸው ፕሬዝደንቱ ሁለት መልዕክቶችን አከታትለው ለጠፉ።

ግዙፉ ማሕበራዊ ድር አምባ የትራምፕ ትዊቶች የኩባንያውን ፖሊሲ የሚጥሱና አመፅ የሚያነሳሱ ናቸው ሲል እስከወዲያኛው አሰናበታቸው።

ትራምፕ ከትዊተር ብቻ ሳይሆን ከፌስቡክ፣ እንዲሁም የጌም ማዕከል ከሆነው ትዊች እና ከስናፕቻትም ታግደዋል።