ፋሽን ፡ ለሚስታቸው 'የሥራ ሕይወት' ሲሉ የሥራ መልቀቂያ ያስገቡት የግዙፉ ልብስ አምራች ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, ZALANDO
በአውሮፓ ትልቁ የበይነ መረብ ልብስ ቸብቻቢ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሚስታቸው ቅድሚያ ለመስጠት ሲሉ ሥራቸውን እንደሚለቁ አስታውቀዋል።
"የሚስት ሙያ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
ሩቢን ሪተር፤ ዞላንዶ የተባለው ልብስ አምራችና ሻጭ ኩባንያ ባለቤት ሆነው ለ10 ዓመታት አገልግለዋል።
ከ12 ዓመታት በፊት በጀርመኗ በርሊን ከተማ በትንሽዬ ልብስ መኪና ሥራ የጀመረው ኩባንያ አሁን 36 ሚሊዮን ደንበኞች አሉት።
ኩባንያው ባለፈው ዓመት ብቻ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳጋበሰ አስታውቆ ነበር።
ሥራ አስኪያጁ እስከ 2023 [በፈረንጆቹ] የሚያቆይ ውል ቢኖራቸውም በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ላይ ከመንበሬ እወርዳለሁ ብለዋል።
"ባለቤቴ እና እኔ በሚቀጥሉት ዓመታት የሷ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተስማምተናል" ብለዋል ሥራ አስኪያጅ ሪተር በለቀቁት መግለጫ።
"አሁን ጊዜ ልሰጠው የምፈልገው ጉዳይ ቤተሰብ ነው። ላለፉት 11 ዓመታት ዞላንዶ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነበር። አሁን ግን አቅጣጫዬን መቀየር ያሻኛል" ይላል መግለጫው።
መግለጫው ስለ ሥራ አስኪያጁ ባለቤትም ሆነ ምን እንደሚሰሩ ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ ግዙፉን የልብስ አምራች ኩባንያ ማብራሪያ ቢጠይቅም እስካሁን ምላሸ አላገኘም።
የድርጅቱ ሌሎች ሁለት ጣምራ አስተዳዳሪዎች ሮበርት ዤንትዝ እና ዳቪድ ሽናይደር ኩባንያው እያስተዳደሩ እንደሚቆዩ ተነግሯል።
በ17 ሃገራት የፋሽንና የውበት ምርቶችን የሚቸበችበው ድርጅት ኃላፊ የምርቶችን ጥራት ለማሳደግ ብዙ እንደለፉ ይነግራላቸዋል።
የድርጅቱ ቦርድ ኃላፊዎች ሁሉም ወንዶች ናቸው።
አልፎም ዞላንዶ ለወንዶች ከሴቶች 22 በመቶ ከፍ ያለ ደሞዝ ይከፍላል። ይህ ደግሞ ከሃገሪቱ አማካይ ክፍያ ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ ነው።
ነገር ግን አሁን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቀት እየተዘጋጁ ያሉት ሪተር ድርጅቱ በ2023 በፆታ የተመጣጠነ አስተዳደር ለማዋቀር እየሰራ ነው ብለዋል።
ሥራ አስኪያጁ ስትራቴጂ በመቅረፅ፣ የሕዝብ ግንኙነት በማሳለጥ እንዲሁም የፋይናንስ ክፍልን ሲመሩ ቆይተዋል።












