ሚኒስትሩ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጉቦ በመቀበል ተከሰሱ

ፈተሻ የሚያደርጉ ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኢንዶኔዢያ ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለተቸገሩ ሰዎች ከሚከፋፈል እርዳታ ጋር በተያያዘ ጉቦ ሲቀበሉ ነበር በሚል ክስ ቀረበባቸው።

ሚኒስትሩ ጁሊያሪ ባቱባራ ለተቸገሩ ዜጎች የምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ገንዘብ በመቀበል ነው ክስ የቀረበባቸው።

የአገሪቱ የጸረ ሙስና መስሪያ ቤት በሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ባደረገው ፍተሻ 14.5 ቢሊየን ሩፒያ ወይም 1 ሚሊየን ዶላር በሳምሶናይት እና ሌሎች ማሸጊያዎች ተከማችቶ አግኝተዋል ተብሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቅዳሜ ዕለት በተደረገው ድንገኛ ኦፐሬሽን አራት ተጠርጠሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ትናንት ደግሞ ሚኒስትሩ ጁሊሪያ ባቱባራ እጃቸውን ለፖሊስ ሰጥተዋል።

''ገንዘቡ በሰባት ሳምሶናይቶች ውስጥ ተደርጎ ነበር። በተጨማሪም በሶስት የጀርባ ሻንጣዎች እና በፖስታ ማሸጊያዎች ጭምር ተቀምጧል'' ሲሉ የአገሪቱ የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኃላፊ ፊርሊ ቡሃሪ በመግለጫው አስታውቀዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አገኘሁት ባለው መረጀ መሰረት ደግሞ የጸረ ሙስና ሰራተኞቹ በድንገት ፍተሻ በሚያደርጉበት ወቅት ሚኒስትሩ ከእያንዳንዱ የእርዳታ ካርቶን 10 ሺ ሩፒያህ እንደሚሰጧቸውና ለማንም እንዳይናገሩ ጠይቀዋል።

የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ እስከ 20 የሚደርስ እስርና አንድ ቢሊየን ሩፒያህ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል ሁለቱ መንግስት ኃላፊዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሰዎች ግን ተራ ዜጎች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢንዶኔዢያው ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ደግሞ እሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ሚኒስትሮች ከእንደዚህ አይነት የሙስና ወንጀል እንዲርቁ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃቸውንና ሙሰኞችን እንደማይታገሱ አስታውቀዋል።

''ይህ የህዝቡ ገንዘብ ነው፤ በኮቪድ-19 ጉዳት ለደረሰባቸው ድጋፍና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ተብሎ የታቀደ ነው' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።