የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን የሚቀጣ ሕግ ያወጡት ፖለቲከኛ ድርጊቱን ሲፈፅሙ ተያዙ

ሃንጋሪያዊው ፖለቲከኛ ጆሴፍ ስዛዬ

የፎቶው ባለመብት, European Parliament

ሃንጋሪያዊው ፖለቲከኛ ጆሴፍ ስዛዬር በዚህ ሳምንት በአውሮፓ ስማቸው የመገናኛ ብዙሃን አፍ መፍቻ ሆኖ ከርሟል።

ነገሩ ወዲህ ነው። ሰውዬው ቤልጂየም ውስጥ የኮሮናቫይረስ ሕግጋትን ጥሰው በቁጥጥር ሥር ይውላሉ።

ነግር ግን አነጋጋሪ የነበረው ነገር በዘመነ ኮቪድ ለምን 25 ሰዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ተገኙ የሚለው አልነበረም።

ሰውዬው ሃንጋሪ ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅር በሕገ-መንግሥት እንዲከለከል ሕግ ያረቀቁ ናቸው።

ነገር ግን እጅ ከፍንጅ የተያዙ ከሌሎች ወንዶች ጋር ራቁታቸውን ሲጨፍሩ፣ ሲበሉ ሲጠጡ እንዲሁም የአገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው የወሲብ ፓርቲ እየተካሄደበት ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ሰው ፖሊስ እጃችሁን ወደላይ ሲል በአጥር ዘለው ሊያመልጡ ሲሞክሩ ተይዘዋል።

ሰውዬው ከተያዙ በኋላ ይህ የኔ ችግር እንጂ ከሃገሬ ጋር ወይም ከፖለቲካ ምህዳሩ ጋር ምንም አይገናኝም ብለዋል።

ስዛዬር፤ ሃንጋሪ ውስጥ የወግ አጥባቂውና አምባገነኑ የፊደስ መንግሥት መሥራች ናቸው።

ፊደስ ሃንጋሪ ውስጥ አውራ ፓርቲ ነው።

ፓርቲው የተቃዋሚ አባላት ድምፆችን በማፈን ይታወቃል። አልፎም ሕገ ውጭውን አካል ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር አፋኝ ሕጎች ያረቃል።

ፓርቲው ከሌሎች የአውሮፓ ሕብረት በተለየ የተመሳሳይ ፆታ ፍቅርን የሚቀጣ ሕግ አውጥቷል።

በፅንስ ማስወረድ ረገድም አከራካሪ ሕግ ያላት ናት ሃገረ ሃንጋሪ።

በሃንጋሪ ሕግ ጋብቻ የሚፈቀደው በወንድና በሴት መካከል ብቻ ነው የሚለውን አንቀፅ የፃፉት በተመሳሳይ ፆታ ፓርቲ ላይ የተገኙት ጆሴፍ ናቸው።

ልክ ይህ መረጃ ሲወጣ ፖለቲከኛው ከአውሮፓ ፓርላማ አባልነት ራሱን አግልሏል።

ተንታኞች የሰውዬው የፖለቲካ ሕይወት አበቃለት እያሉ ይገኛሉ።

የፊደስ ፓርቲ ሊቀ መንበርና የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የፖለቲካ አጋራቸውን ጉድ ሲሰሙ ከዚህ በፊት ላደረገው እናመሰግነዋለን ከዚህ በኋላ ግን ብቻውን ነው የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት ሰጥተዋል።

ቤልጂዬም ውስጥ ፓርቲውን ያዘጋጁት ሰው ፖሊስ ዘለፋ አድርሶብናል ሲሉ አማረዋል።

"ፖሊስ መታወቂያችሁን አሳዩን ይላል። ሰው ሁሉ ራቁቱን ነው። አንዴት አድርገን ነው መታወቂያ የምናሳዬው" ብለዋል።

ፖለቲከኛው የኮቪድ-19 ሕግጋት በመጣሳቸው ይቀጣሉ ተብሏል።