አርጀንቲና በወረርሽኙ የተጠቁትን ለመደጎም የናጠጡ ኃብታሞቿ ላይ ግብር ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አርጀንቲና አገሯ በሚገኙ የናጠጡ ኃብታሞች ላይ ለየት ያለ ግብር ጥላለች።
ግብሩ ለኮሮናቫይረስ የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶች ግብዓትና በወረርሽኙ ምክንያት ክፉኛ ለተጠቁት ኑሯቸውን መደጎሚያ እንዲሆን ነው።
የምክር ቤቱ አባላት "የሚሊዮነሮች ግብር" ብለው የጠሩት በአንዴ የሚከፈል ገንዘብ ሲሆን በዚህ ሳምንት አርብም 42 ለ 26 በሆነ የድምፅ ብልጫም ፀድቋል።
በዚህም መሰረት ከ200 ሚሊዮን ፔሶ (2.5 ሚሊዮን ዶላር) ኃብት ያከማቹ ግለሰቦች መክፈል አለባቸው።
በአገሪቱ ይህ የገንዘብ መጠን ያላቸውም ወደ 12 ሺህ ግለሰቦች ናቸው ተብሏል።
አርጀንቲና በወረርሽኙ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ስትሆን እስካሁን ባለውም መረጃ 1.5 ሚሊዮን በቫይረሱ ሲያዙ 40 ሺህ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
የህዝብ ቁጥሯ 45 ሚሊዮን ብቻ የሆነው አርጀንቲና በወረርሽኙ በሚሊዮኖች በተያዙ ተርታ አምስተኛ ደረጃን ይዛለች። ከህዝብ ቁጥሯ ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከሚሊዮን በላይ ካስመዘገቡ ትንሿ አገር አድርጓታል።
ወረርሽኙን ለመግታት ያስቀመጠቻቸው መመሪያዎች ከፍተኛ ተፅእኖን አሳርፈዋል። በስራ አጥነት፣ በርካታዎች በድህነት ወለል በሚኖሩባትና አገሪቷ ራሷ በብድር በተዘፈቀበችበት ሁኔታ መመሪያዎቹ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነዋል።
አርጀንቲና ከ2018 ጀምሮም በምጣኔ ኃብት ድቀት ላይ ናት።
የሚሊዮነሮችን ግብር ካረቀቁት መካከል አንዱ ህጉ 0.8 በመቶ የሚሆነውን ግብር ከፋይ ብቻ ነው የሚመለከተው ብለዋል።
በአርጀንቲና ውስጥ ያሉት ሃብታሞች፣ ከአንጡራ ሃብታቸው 3.5 በመቶ እንዲሁም ከአገር ውጭ ያሉ አርጀንቲናውያን ደግሞ 5.25 በመቶ እንዲከፍሉ ውሳኔ ተላልፏል።
ከግብሩ የተሰበሰበው ገንዘብም መካከል 20 በመቶ ለህክምና ቁሳቁሶች፣ 20 በመቶ ለጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች፣ 20 በመቶ ለተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ፣ 15 በመቶ ለማህበራዊ ልማትና ቀሪው 25 በመቶ ደግሞ ለተፈጥሮ ነዳጅ ስራዎች እንደሚውል ኤኤፍፒ በዘገባው አስነብቧል።
ግራ ዘመሙ ፕሬዚዳንት አልበርቶ ፈርናንዴዝ መንግሥት 300 ቢሊዮን ፔሶም ለማሰባሰብ እቅድ ይዘዋል።
ሆኖም የተቃዋሚዎች ፓርቲ ቡድኖች በበኩላቸው ይህ የአንድ ጊዜ ግብር ሊሆን ስለማይችል የውጭ አገራት ኢንቨስትሮችን ፍራቻ ላይ ይጥላል በማለት ተችተዋል።
የቀኝ ክንፍ ፓርቲ ጁንቶስ ፖር ኤል ካምቢዮ በበኩሉ የማይገባ ሲል የፈረጀው ሲሆን "ነጠቃም" ነው ብሎታል።












