ሕንድ ውስጥ በርካቶች ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ታመው ሆስፒታል ገቡ

የመንገድ ዳር ሻይ ሻጮች

የፎቶው ባለመብት, Alamy

በሕንድ ውስጥ በሚገኝ አንድ ግዛት ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ምንነቱ ባልታወቀ በሽታ ታመው ሆስፒታል መግባተቸው ተነገረ።

የአገሪቱ ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ 140 ሰዎችን ሆስፒታል እንዲገቡ ያደረገው በሽታን ምንነት ለማወቅ ምርምራ እያካሄዱ ነው።

የህክምና ተመራማሪዎችም የዚህን በሽታ ምንነት ለመለየት እና የሕመሙን መንስኤ ለማወቅ ጥረት መጀመራቸው አስታውቀዋል።

አንድራ ፕራዴሽ ከሚባለው ግዛት የመጡት ታማሚዎች በርካታ የተለያዩ የሕመም ምልክቶች ሲያሳዩ የነበረ ሲሆን፤ ከምልክቶቹ ውስጥም ማቅለሽለሽ እና እራስን ስቶ ተዝለፍልፎ መውደቅ ደግሞ አብዛኛዎቹ ላይ የተስተዋለ እንደሆነ ዶክተሮች ገልጸዋል።

ኢሉሩ የተባለው የመንግሥት ሆስፒታል ደግሞ ምናልባት ተጨማሪ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች ከመጡ በሚል በርካታ አልጋዎች ነጻ ሆነው እንዲጠባበቁም ተደርጓል ተብሏል።

ሕንድ የኮሮናቫይረስ ተጽእኖን ለመቀነስ እና ስርጭቱን ለመቆጣጠር ደፋ ቀና በምትልበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ምንነቱ ያልታወቀ ሕመም መከሰቱ በርካቶችን አሳስቧል።

የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ደግሞ ሁሉም ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ታማሚዎች የኮሮናቫይረስ ምርምራ የተደረገላቸው ሲሆን ማናቸውም ግን በቫይረሱ አልተያዙም።

በኢሉሩ የመንግሥት ሆስፒታል የሚሰራ አንድ የጤና ባለሙያ ለኢንዲያን ኤክስፕረስ ሲናገር '''አይናችን አካባቢ ማቃጠል ይሰማናል' ብለው ወደ ሆስፒታላችን ከመጡት መካከል በተለይ ደግሞ ሕጻናቱ ወዲያው ማስመለስ ጀመሩ። አንዳንዶቹ እራሳቸውን የሳቱ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ቅዝቃዜ ተሰምቷቸው ይንቀጠቀጡ ነበር'' ብሏል።

ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን አንዳንዶቹም ተሽሏቸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ መደረጉ ተገልጿል።

የአንድራ ፕራዳሽ የጤና ሚኒስትር አላ ካሊ ካሊ ክሪሽና እንዳሉት ደግሞ ከሁሉም ታማሚዎች ላይ የደም ናሙና የተወሰደ ቢሆንም ምንም አይነት የቫይረስ ኢንፌክሽን ምልክት ግን አልታየባቸውም።

''ባለሙያዎቻችን የሰዎቹን መኖሪያ አካባቢ ከጎበኙ በኋላ በምርመራችን የአየር እና የውሃ ብክለት አለመሆኑን ደርሰንበታል። ምስጢራዊ የሆነ ሕመም ይመስላል፤ የትኛውም የላብራቶሪ ምርመራ ምክንያቱን ሊያውቀው አልቻለም'' ብለዋል የጤና ሚንስትሩ።