ቅርጫት ኳስ ፡ የኦባማ እና የጆርዳን የቅርጫት ኳስ መለያዎች በከፍተኛ ገንዘብ በጨረታ ተሸጡ

በከፍተኛ ገንዘብ የተሸጡት የማይክል ጆርዳንና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መለያዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በከፍተኛ ገንዘብ የተሸጡት የማይክል ጆርዳንና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ መለያዎች

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማና በታዋቂው የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ኮከብ ማይክል ጆርዳን የተለበሱ ሁለት የቅርጫት ኳስ መለያዎች አርብ ዕለት ሎስ አንጀለስ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ጨረታ ክብረ ወሰን ነው በተባለ ከፍተኛ ገንዘብ ተሸጡ።

ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ማይክል ጆርዳን በ1984 (እአአ) ለቺካጎ ቡልስ ቡድን ለመጫወት በፈረመበት ጊዜ የለበሰው ባለ 23 ቁጥር መለያ ለጨረታ ቀርቦ 320 ሺህ ዶላር ተሽጧል።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ለትምህርት ቤታቸው ፑናሁ ቡድን በተጫወቱበት ጊዜ ለብሰውት የነበረው መለያ ደግሞ በ192 ሺህ ዶላር ሲሸጥ፤ ይህም በጨረታ ከተሸጡ የተማሪዎች መለያ ከፍተኛውን ዋጋ አውጥቷል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደ ጨረታ ኦባማ ተማሪ ሳሉ ለብሰውት የነበረ ሌላ የቅርጫት ኳስ መለያ በ120 ሺህ ዶላር ተሽጦ ነበር።

በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው የኦባማ መለያ የትምህርት ቤታቸው ቡድን በ1979 (እአአ) የሃዋይ የቅርጫት ኳስ ውድድርን ባሸነፈበት ጊዜ ለብሰውት የነበረው ባለ 23 ቁጥር መለያ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ለቅርጫት ኳስ ስፖርት ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ሲሆን፤ በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ የተፎካካሪ ቡድን አባላት ወላጆች ተገቢ ያልሆነ የበላይነትን እንዲያገኙ አድርገዋል በሚል ቅሬታ በማሰማታቸው ልጃቸው ሳሻ የምትጫወትበትን የቅርጫት ኳስ ቡድን ማሰልጠን እንደተዉ ጽፈዋል።

የመጀመሪያው ቢሊየነር ስፖርተኛ የሆነው ኮከቡ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ጆርዳን ቡድኑ ቺካጎ ቡልስ በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ውድድር የበላይ ሆኖ ስድስት ጊዜ አሸናፊ ለመሆን አስችሎታል።

የጆርዳን መለያዎች በተለያዩ ጊዜያት በጨረታ የተሸጡ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት ከተሸጡ 23 ቁጥር መለያዎች ከፍተኛው 288,000 ዶላር ነበር።