ኮቪድ-19 ፡ ጆ ባይደን አሜሪካውያን ክትባትን እንዲወስዱ አይገደዱም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካን ምርጫ ያሸነፉት ተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሜሪካውያን የኮቪድ-19 ክትባትን የመውሰድ ግዴታ የለባቸውም አሉ።
ወረርሽኙ በአገሪቱ ከፍተኛ የስርጭት ደረጃ መድረሱን የገለጸው የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ተቋም ሲዲሲ፤ አሜሪካውያን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ በጥብቅ አሳስቧል።
ያሳለፍነው አርብ ብቻ 2,500 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል። 225 ሺህ ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።
በአሜሪካ ውስጥ እስካሁን 14.3 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው 278,000 ዜጎች ሞተዋል።
ጆ ባይደን በወረርሽኙ ሳቢያ ስልጣናቸውን በሚረከቡበት በዐለ ሲመታቸው ላይ በርካታ ሰው እንደማይገኝ አስታውቀዋል።
95 በመቶ ውጤታማ ነው የተባለው የፋይዘር እና 94 በመቶ ውጤት አስመዝግቧል የተባለው የሞደርና የኮቪድ-19 ክትባቶች አሜሪካ ውስጥ ፍቃድ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ለፋይዘር ክትባት ፍቃድ የሰጠች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ማይክ ፔንስ ያለፈው ሳምንት "የኮቪድ-19 ክትባት አንድ ሳምንት ተኩል ገደማ ይቀረዋል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ባይደን በበኩላቸው ዜጎች ክትባቱን እንዲወስዱ ማስገደድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል ብለዋል።
"ባለኝ አቅም ሁሉ ሰዎች ትክክለኛው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እገፋፋለሁ። ውሳኔያቸውንም አከብራለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
የባይደን አቋም ምንድን ነው?
ፒው የተባለ የጥናት ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው 60 በመቶ አሜሪካውያን ክትባት ለመውሰድ ዝግጁ ናቸው። መስከረም ላይ ክትባት እንወስዳለን ያሉት 51 በመቶው ብቻ ነበሩ።
ባለፈው ሳምንት ባይደን በሕዝብ ፊት ክትባት እንደሚወስዱ ለሲኤንኤን ቴሌቪዥን ተናግረዋል። ይህም ክትባት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ሐሳባቸውን ቀይረው ክትባቱን እንዲያምኑ ለማበረታታት ነው።
በሕዝብ ፊት እንከተባለን ካሉት መካከልም የቀድሞዎቹ የአሜሪካ መሪዎች ባራክ ኦባማ፣ ጆርጅ ቡሽ እና ቢል ክሊንተን ይገኙበታል።
ሰዎች ላይ ጫና ማሳደር የሚፈለገውን ውጤት ላያመጣ እንደሚችል የሚያምኑት ባይደን፤ መንግሥት ዜጎች እንዲከተቡ ማስገደድ የለበትም የሚል አቋም ነው ያላቸው።
ተንታኞች እንደሚሉት፤ ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ ሲገደዱ ጉዳዩ ከጤና አጀንዳነት ወደ ፖለቲካ አቋምነት ተቀይሯል።
ክትባት መውሰድን ግዴታ በማድረግ ተመሳሳይ አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ሰዎች በፍቃዳቸው እንዲያደርጉት መተው እንደ አማራጭ ተወስዷል።
ባይደን በዋነኛነት ክትባቱን እንዲወስዱ የሚያበረታቱት የጤና ባለሙያዎችን እና አረጋውያን የሚንከባከቡ ባለሙያዎችን ነው።
















