ኮሮናቫይረስ ፡ አሜሪካ ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 195 ሺህ ሰዎች ኮቪድ-19 ተገኘባቸው

አሜሪካ ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 195 ሺህ ሰው በኮቪድ-19 ተገኘባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከጀመረ ወዲህ በአንድ ቀን ብቻ ከፍተኛ የተባለውን ቁጥር አስመዝግባለች። ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ታማሚዎች ቁጥርም ጣራ ነክቷል።

በኮቪድ-19 ምክንያት የአሜሪካ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ሆኗል። ይህም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ማለት ነው።

ረቡዕ ዕለት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ 195 ሺህ 695 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

2 ሺህ 733 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአንድ ቀን ሕይወታቸው አልፏል።

የሎስ አንጀለስ ከተማ ወረርሽኙ እንደ አዲስ በማገርሸቱ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ አዛለች።

በአሜሪካ በጠቅላላው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ሚሊዮን ገደማ ሆኗል። የሟቾች ቁጥር ደግሞ 254 ሺህ ነው።

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መጥቷል።

ባለፈው ወር በየሳምንቱ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ ተዘግቧል።

ይህን ተከትሎ የሃገሪቱ የጤና ሥርዓት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የጤና ሙያተኞች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።

ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው ካሊፎርኒያ፣ ቴክሳስና ፍሎሪዳ ግዛቶች በቫይረሱ እጅጉን ከተጠቁ መካከል ናቸው።

የሎስ አንጀለስ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ ግራሴቲ ወዲያውኑ ተግባራዊ የሚደረግ የቤት ውስጥ ተቀመጡ አዋጅ ከተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካውያን ለገና እና ተያያዥ በዓላት ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩበት ወቅት ስለሆነ የወረርሽኙ መስፋፋት ቢጨምርም እንጂ አይቀንስም የሚል ስጋት አላቸው።

የአሜሪካ በሽታ መቆጣጠር ማዕከል ነዋሪዎች በገና በዓል ሲሉ ከመጓጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ነገር ግን ማዕከሉ ከዚህ በፊት ሰዎች ኮሮናቫይረስ ካለበት ሰው ጋር ግንኙት ካላቸው 14 ቀናት ራሳቸውን ያገላሉ ሲል ያወጣውን ጥብቅ ትዕዛዝ በማላላት ወደ 7 ዝቅ አድርጎታል።

የአሜሪካ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣናት ሞደርና የተባለው ክትባት ለተጠቃሚዎች መሰራጨት ይችላል ወይስ ገና ነው የሚለውን ለመወሰን ለታህሳስ 10 ቀጠሮ ይዘዋል።

ታህሳስ 17 ደግሞ ፋይዘር የተባለው ተቋም ያመረተውን ክትባት ለመፈተሽ ይገናኛሉ።

ዩናይትድ ኪንግደም ፋይዘር የተሰኘው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከዓለም ቀዳሚዋ ሆናለች።

በአሜሪካም ክትባቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ከተገኘ 21 ሚሊዮን የሚሆኑ የጤና ተቋማት ሠራተኞች ክትባቱ ቀድሞ ይደርሳቸዋል ተብሏል።

በመቀጠል ደግሞ 3 ሚሊዮን የዕድሜ ባለፀጋዎች ማቆያ የሚኖሩ አዛውንት ክትባቱን ያገኛሉ የሚል ተስፋ አለ።

የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ያሳሰባቸው ሌላው ጉዳይ ምን ያክል አሜሪካውያን ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ ይሆናሉ የሚለው ጉዳይ ነው።

በቅርቡ የተሰበሰበ አንድ ጥናት 58 በመቶ ሰዎች ክትባቱን ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናቸውን ያሳያል።