ስፖርት፡ የታዋቂው ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን ጫማ በ23 ሚሊዮን ብር በጨረታ ተሸጠ

በ23 ሚሊዮን ብር በጨረታ የተሸጠው የማይክል ጆርዳን ናይክ ኤይር ጆርዳን ስኒከር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ23 ሚሊዮን ብር በጨረታ የተሸጠው የማይክል ጆርዳን ናይክ ኤይር ጆርዳን ስኒከር

ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን የተጫማው ጫማ 615 ሺህ ዶላር (23 ሚሊዮን ብር በሚገመት) በጨረታ ተሸጧል።

በዚህ ሳምንት በበይነ መረብ በነበረው ጨረታ ላይ ናይክ ኤይር ጆርዳን 1 የተባለው የስፖርተኛው ጫማ መሸጡም ተገልጿል።

ጫማውም በቺካጎ ቡልስ ቡድን ይጫወት በነበረበት ወቅት በጎርጎሳውያኑ 1985 ያጠለቀው ነው ተብሏል።

በዚህ ጫማም ወደላይ በመዝለል በርካታ ኳሶችን በመረቡ በማስቆጠርም በታሪካዊነቱ የተመዘገበ ነው።

በርካታ ስፖርታዊና የስነ ጥበብ ጨረታዎችን በማካሄድ የሚታወቀው ክርስቲስ የተባለው ኩባንያ እስካሁን ድረስ ዘጠኝ የማይክል ጆርዳን ጫማዎችን ሸጧል።

እነዚህ ጫማዎችም ማይክል ጆርዳን ለአስራ አራት አመታት የነገሰበትን የቺካጎ ቡልስ ቡድን ቆይታውን ለመዘከርም ነው።

ጫማው ስታዲየም ጉድስ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ንብረት ሲሆን፤ ከማይክል ጆርዳን ታሪካዊ ጫማዎች ውስጥ ምርጡም ነው ተብሏል።

ሁሉም ጫማዎች ማይክልን ስፖንሰር ያደርገው በነበረው ናይኪ የአልባሳትና ጫማ አምራች ኩባንያ የተመረቱ ናቸው።

ብርቅና ድንቅ የተባለውን ይህንን ጫማ ጨምሮ ሌሎች ጫማዎችን መሰብሰብ የሚፈልጉ ስላሉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስም እየሸመቱ መሆናቸውንም ኩባንያው አስታውቋል።

ከዚህ ጫማም በተጨማሪ በጎርጎሳውያኑ 1992 ኦሎምፒክስ ላይ አሜሪካን ለድል ያበቃትን ጨዋታ የተጫወተብትን ኤይር ጆርዳን 7 በ11 ሺህ 500 ዶላር (413 ሺህ ብር) ተሸጧል።

ሌሎች ስብስቦችም እንዲሁ በ21 ሺህ 500 ዶላርና (772 ሺህ ብር)፣ 8 ሺህ 750 ዶላር (314 ሺህ) ለሽያጭ ቀርበዋል።

በገበያው ላይ ያለው ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜም እየጨመረ መሆኑንም ኩባንያው አመላክቷል።

ማይክል ጆርዳን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርጫት ኳስ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ማይክል ጆርዳን የቅርጫት ንጉስና ድንቅ ተጫዋችም ተብሎ ይሞካሸል።

በአለም ስፓርትም ዘንድ ከፍተኛ ዝናን የተጎናፀፈው ማይክል በተለይም በጎርጎሳውያኑ 1980ዎቹና 90ዎቹ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን በአለም አቀፉ መድረክ በማስተዋወቅ ረገድም ሚናን በመጫወቱም ስሙ ይወሳል።

በቅርቡ በስፖርተኛው ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጠነው 'ዘ ላስት ዳንስ' የሚል ርዕስ የተሰጠውም ተከታታይ ፊልም በኔትፍሊክስ መውጣቱን ተከትሎ የማይክል ጆርዳን ዝናም እንደገና እየተነሳ ይመስላል።