ሐይማኖት ፡ የክርስቶስ ምስል ላይ የተፋው እስራኤላዊ ከሥራው ተባረረ

የእስራኤል አምቡላንስ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ እስራኤላዊ የሕክምና ሠራተኛ ወደ አንድ ክርስትያን ቤት የኮቪድ ምርመራ ሊያደርግ ሄዶ የክርስቶስ ምስል ላይ ምራቁን በመትፋቱ ከሥራው ተባረረ።

ጃፋ በተባለችው የቴል አቪቭ ግዛት የሕክምና ሥራውን ሲያከናውን የነበረው ግለሰብ በአንድ ግቢ መተላለፊያ ላይ የነበሩ ሦስት ምስሎች ላይ ነው የተፋው ተብሏል።

ይህን ሲያደርግ ያየችው አንዲት ሴት ግለሰቡን ስትጋፈጠው "በሂብሩ መፅሐፍ የጣዖት አምልኮት የተከለከለ ነው " ሲል መመለሱ ተገልጿል።

የእስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት የሰውየውን ድርጊት 'በፅኑ እንደሚያወግዝ' አመልክቶ፤ ግለሰቡ ወዲያውኑ ከሥራው እንደተባረረ ድርጅቱ አስታውቋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ድርጊቱ የተፈፀመው በዕለተ ሰንበት ሲሆን፤ ሰውዬው ክርስትያኖች ወደ ሚኖሩበት ሕንፃ ያመራው ለኮቪድ-19 ምርመራ ነው።

በሕንፃው ላይ የተሰቀለ ካሜራ የሕክምና ባለሙያው የመከላከያ ልብሱን ካወለቀ በኋላ ምስሉ ላይ ሲተፋና ከዚያም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሉን አጥልቆ ወደ አሳንሰር ሲገባ ታይቷል።

ሰውዬው በሕንፃው ከምትኖር አንዲት ሴት ጋር ሲጨቃጨቅ ሴትዬዋ በተንቀሳቃሽ ስልኳ ቀድታ ይዛዋለች።

ለምንድን እንዲህ እንዳደረገ ሴትዬዋ ለጠየቀችው ጥያቄ "በአይሁድ እምነት ይህ የባዕድ አምልኮ ነው" ሲል መልሶላታል።

"እኔ የማምንበት ምስል ላይ ተፍተሃል። ይሄን ደግሞ በካሜራ ይዤዋለሁ። ለምን ይህን አደረግክ?" ስትል የሕንፃው ነዋሪ ሰውዬውን ስትጠይቀው በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ይታያል።

ጉዳዩ ወደ እስራኤል አምቡላንስ አገልግሎት ከተላለፈ በኋላ መሥሪያ ቤቱ ሰውዬው ወዲያውኑ ከሥራው አባሮታል።

መሥሪያ ቤቱ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት የሰውዬውን ድርጊት በፅኑ እንደሚቃወም አስታውቆ ከሁሉም እምነት ተከታዮች ጋር እንደሚሠራና ሠራተኞቹም የተለያየ እምነት ያላቸው እንደሆኑ ፅፏል።

እስራኤል በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ የዓለማችን አገራት አንዷ ናት። አገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደብ ከጣለች በኋላ አሁን እያላላችው ነው።