ሐይማኖት፡ ቤልጂየም ቅዱስ ቁርዓንን ሊያቃጥሉ የነበሩ የዴንማርክ ዜጎችን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቤልጂየም ቅዱስ ቁርዓንን ሊያቃጥሉ የነበሩ አምስት የዴንማርክ ዜግነት ያለቸው የቀኝ አክራሪ ቡድን አባላትን ከአገሯ አባራለች። ለአንድ ዓመትም ተመልሰው ወደ ቤልጂየም እንዳይገቡ እግድ ጥላባቸዋለች።
ለዚህ ቅጣት የተዳረጉት አምስቱ ዴንማርካዊያን ቤልጂየም ውስጥ ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል ሥነ ሥርዓት ለማከናወን መዶለታቸውን ስለደረሰችበት ነው።
አምስቱ ዴንማርካዊያን ይህን ድርጊት ሊፈጽሙ የነበረው በቤልጂየም ሙስሊሞች በሚበዙበት ሰፈር ነበር።
በቤልጂየም የስደተኛ ጉዳዮች ዋና ጸሐፊ ሳሚ ማሕዲ ድርጊቱን ሊፈጽሙ የነበሩትን ዶላቾች "ለሰላምና መረጋጋት አደገኛ ፍጡሮች" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
አምስቱ አክራሪ ቀኝ ዘመም ዴንማርካዊያን የመጤ_ጠል ፓርቲ መሪ የዴንማርካዊው የሚስተር ራስመስ ፓሉዳን ወዳጆች ናቸው።
ራስመስ ፓሉዳን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ጥቁሮችና ሙስሊሞች በሕጋዊነት መኖራቸው ትክክል አይደለም፣ ወደመጡበት መመለስም አለባቸው፣ አውሮፓ የአውሮፓዊያን ናት የሚል ትግል የያዘ ቀኝ አክራሪ ዴንማርካዊ ግለሰብ ነው።
ፓሉዳን ባለፈው ረቡዕ በፓሪስ ቅዱስ ቁርዓንን የማቃጠል ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ፍላጎት እንዳለው በመታወቁ በአስቸኳይ ከፈረንሳይ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል።
በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመርያ ደግሞ ራስመስ ፓሉዳን በአገሩ ዴንማርክ የአንድ ወር እስር ተፈርዶበት ነበር። ለእስር የተዳረገውም በማኅበራዊ ሚዲያው ጸረ ኢስላም ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችን በማሰራጨቱ ነበር።
ራስመስ ሁሉም ሙስሊሞች ከአውሮፓ ሊወጡ ይገባል የሚል አቋም የሚያራምድ ፓርቲ መሪ ነው።
አምስቱ ቤልጂየም ያባረረቻቸው ዴንማርካዊያን የፓሉዳን አጋሮች የነበሩ ሲሆን፤ በርካታ ሞሮኳዊያን ይኖሩበታል በሚባለው በብራስልስ ከተማ ሞልነቢክ ሴይን ዣን ሰፈር ቅዱስ ቁርዓንን ለማቃጠል ሲዶልቱ ነበር ተብሏል።
የቤልጂየም የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ "አሁን እኛ ጥላቻን የሚነዛ ሰው አንፈልግም" ብለዋል።
ባለፈው ነሐሴ የሚስተር ራስመስ ፓሉዳን ደጋፊዎች ከኮፐንሐገን በቅርብ ርቀት በምትገኘውና ስደተኞች በሚበዙባት የስዊድን ሦስተኛ ከተማ ማልሞ፣ ቅዱስ ቁርዓን ለማቃጠል በመሞከራቸው ረብሻ ተቀስቅሶ ብዙ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።












