የሴት ልጅ ጥቃት፡ መደፈርን የምትቃወመው ሊቢያዊቷ ተሟጋች በሽጉጥ ተገደለች

ሃናን አል ባራሲ

የፎቶው ባለመብት, Amnesty

በሊቢያ ውስጥ የመደፈር ጥቃትን በመቃወም የምትታወቀው ተሟጋቿ ሃናን አል ባራሲ በሽጉጥ መገደል ቁጣን ቀስቅሷል።

ሃናን አል ባራሲ በአገሪቷ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው ቤንጋዚ ግዛትም ነው የተገደለችው ተብሏል።

በቤንጋዚ ዋና ጎዳና ላይ በመኪናዋም ውስጥ እያለች እንደተተኮሰባትም ተገልጿል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በፅኑ የምትታወቀው ሃናን አል ባራሲ በሙያዋ ጠበቃም ናት።

በቅርቡም በከተማዋ ላይ ደረሰ የተባለ የመደፈር ጥቃትና ትንኮሳን አጋልጣለች።

የመደፈር ጥቃቱም ሆነ ትንኮሳዎቹ የደረሱት ጄነራል ካሊፋ ሃፍታር ከተባሉትና የአገሪቷን የተወሰነ ክፍል ከተቆጣጠሩት ኮማንደር ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ተዋጊዎች እንደሆነም ይፋ አድርጋ ነበር።

ይህንን ማጋለጧን ተከትሎ በሷም ላይ ሆነ በሴት ልጇ ላይ የሞት ማስፈራሪያዎች ሲደርሳቸው እንደነበር የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ አስታውቋል።

የተሟጋቿ ሞት በሊቢያ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በርካቶችም ፍትህን እየጠየቁ ይገኛሉ።

ለበርካታ አመታት ሊቢያን የገዟት መሪዋ ሙዓመር ጋዳፊን ሞት ተከትሎ አገሪቷ እርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ትገኛለች። በቅርቡም የአገሪቷን የወደፊት አቅጣጫ አስመልክቶ በጎረቤቷ ቱኒዝያ ውይይት በመደረግ ላይ ይገኛል።