ደራሲ ቺማማንዳ የአሸናፊዎች አሸናፊ ተብላ ተሸለመች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ናይጄሪያዊቷ ፀሓፊ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቼ የአሸናፊዎች አሸናፊ ተብላ ተሸልማለች።
ታዋቂ ድርሰቷም 'ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን' (Half of a Yellow Sun) በሴቶች የልብወለድ ድርሰትም በ25 አመታት ውስጥ ያሸነፈው ምርጥ መፅሃፍ ተብሏል።
ደራሲዋ ሽልማቱን በጎሮጎሳውያኑ 2007 ያሸነፈች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ሌሎች ከዚህ ቀደም ሽልማቱን ካሸነፉ 25 ደራሲዎች ጋር ተወዳድራ በህዝብ ምርጫም ማሸነፍ ችላለች።
ከዚህ ቀደም ሽልማቱን ማሸነፍ የቻሉት ዛዲ ስሚዝ፣ በህይወት የሌለችው አንድሪያ ሌቪ፣ ሊዮኔል ሽሪቨር፣ ሮዝ ትሪሜይንና ማጊ ኦ ፋሬል ናቸው።
ይህ ሽልማት ከዚህ ቀደም ኦሬንጅና ቤይሊስ ሽልማቶች በመባልም ይታወቃል።
'ሃፍ ኦፍ ኤ የሎው ሰን' መቼቱን ያደረገው በናይጄሪያ ሲሆን ባይፋሪያን ጦርነት ላይ ያጠነጠነ ነው።
ድርሰቱም ቅኝ ግዛት፣ የብሔር ታማኝነት፣ መደብ፣ ዘር እንዲሁም የሴቶችን ብቃት ይዳስሳል።
በጎሮጎሳውያኑ 2006 የወጣው ይህ መፅሃፍ በአለም አቀፉ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና መወደድን አትርፏል።
መፅሃፉ ወደ ፊልምም በጎሮጎሳውያኑ 2013 ተቀይሯል።
"የአሸናፊዎች አሸናፊ ተብዬ መመረጤ በጣም ከፍተኛ ደስተኛ ነኝ። ከዚህ ቀደም ይሄ ሽልማት በአለም አቀፉ ዘንድ ከፍተኛ አንባቢን ፈጥሮልኛል፤ በርካታ ድንቅ ፀሃፊዎችንም ስራዎች አሳውቆኛል" በማለት ቺማማንዳ ተናግራለች።
ከ8 ሺህ 500 ሰዎች በላይ አንባቢያን ድምፃቸውን በመስጠት የመረጡም ሲሆን በርካቶችም በሽልማቱ የዲጂታል ቡክ ክለብ ተጋብዘው አስተያየቶቻቸውን አጋርተዋል።












