ሴኔጋል፡በስደት ሰምጦ የሞተው ታዳጊ አባት በቁጥጥር ስር ዋለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሴኔጋል ወደ አውሮፓ በማቅናት ላይ እያለ ባህር ውስጥ ሰምጦ የሞተው ታዳጊ አባት በቁጥጥር ስር ውሏል።
ታዳጊው የ15 አመት ሲሆን ባለፈው ወርም ነው ወደ አውሮፓ ያቀናው።
አባትየው ልጁን ወደ ስፔን እንዲወስዱት ለህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች 450 ዶላር ከፍሏልም ተብሏል።
ከስፔንም በመቀጠል ወደ ጣልያን ተወስዶ እግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከልም እንዲገባ እቅድ ተይዞ ነበር።
በቅፅል ስሙ ዱዱ ተብሎ የሚጠራው ታዳጊ አውሮፓ ሳይደርስ የሞተ ሲሆን አስከሬኑም ወደ ባህሩ እንደተጣለ ተነግሯል።
የታዳጊው ሞት በሴኔጋል ኃዘን የፈጠረ ሲሆን፤ በቅርቡም ከምዕራባዊቷ አገር ተነስተው ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚሞክሩ ሴኔጋላውያን ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው ተብሏል።
በርካቶችም ፈታኝ የሆነውን ባህርና ውቅያኖስ እንደሚሻገሩም ተገልጿል።
የሴኔጋል ፖሊስ እንዳለው በቅርቡ ብቻ ከ1 ሺህ 500 በላይ ስደተኞችን መመለስ እንደቻለም አሳውቋል።












