ቲክቶክ የትራምፕ አስተዳደር ላይ የክስ ሂደት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይናው የቪዲዮ ማህበራዊ መተግበሪያ ቲክቶክ ከህዳር 3/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማድረግ የታሰበውን እቅድ በመቃወም ቲክቶክ በትራምፕ አስተዳደር ላይ የክስ ሂደት ጀምሯል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ባይትዳንስ እስከ ህዳር 3/ 2013 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ ድርጅት የማይገዛ ከሆነ ጥቅም ላይ እንዳይውል ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ቲክቶክ በአሜሪካ የሚኖረው የወደፊት እጣ ፈንታ ግልጽ አይደለም። በቻይናው ኩባንያ ባይቴንዳንስ ባለቤትነት የሚተዳደረው ቲክቶክ ለአሜሪካ ብሔራዊ ስጋት ነው የሚል ክስ ይቀርብበታል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ባይቴንዳንስ የአሜሪካውያንን ግላዊ መረጃ እየሰበሰበ ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ያቀርባል ይላል።
ባይቴንዳንስ በበኩሉ የመተግበሪያው ተጠቃሚ ሰዎች መረጃ በአሜሪካ እና በሲንጋፖር የሚከማች መሆኑን እና ለቻይና ሕጎች ተገዢ አለመሆኑን ይጠቅሳል።
ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ለአሜሪካ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ድርሻውን ለመሸጥ ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለቀ ሰዓት ሽያጩ ከሽፏል፡፡
ማይክሮሶፍት ቲክቶክን ለመግዛት ጣጣውን እየጨረሰ ነበር፡፡ ባለቀ ሰዓት ትናንት በምን ምክንያት እንደሆነ ባይታወቅም ሽያጩ ተፋርሷል፡፡
''እስካሁን ድረስ በአሜሪካ ሕግ መሰረት ማድረግ የሚገባውን እና ግልጽ መሆን ያለባቸውን ጉዳዮች በሙሉ በፈቃደኝነት ሲያካሂድ ነበር። ላለፉት ሁለት ወራትም ነገሮች እንደሚስተካከሉ በተስፋ ስንጠባበቅ ነበር'' ብሏል ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ።
'' ፕሬዝዳንቱ ከተጠቃሚዎች ጋር በተያያዘ የገለጹት ስጋት ተገቢ እንዳልሆነ እና ምንም ነገር እንደሌለ ለማሳየት የተቻለንን በሙሉ ስናደርግ ነበር። ከግላዊነትና ደህንነት ጋር የተያያዙ የአገሪቱ ፖሊሲዎች ጋር ተጣጣጣመ አሰራርም ተከትለናል'' ይላል የድርጅቱ መግለጫ።
ድርጅቱ አክሎም 'መብታችንን ለማስከበርና በአሜሪካ የሚገኙ ከ15 ሺ በላይ ሰራተኞቻችንን ጥቅም ለማስከበር' በፍርድ ቤት በኩል ክስ መስርተናል ሲል አስታውቋል።












