ባለ 14 ካራት ትንሽዬ አልማዝ በ26 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ለማግኘት በጣም ከባድና ውድ የተባለ አንድ ሐምራዊ አልማዝ ክብረ ወሰን በሚባል ዋጋ ተሸጠ። ይህ አልማዝ የተሸጠው በጨረታ ሲሆን ጨረታው ስዊዘርላንድ አገር ነው የተካሄደው።
14.8 ካራት የሚመዝነው ይህ አልማዝ "ዘ ስፕሪት ኦፍ ሮዝ" የሚል ስም ተሰጥቶታል። እስከዛሬም ለጨረታ ከቀረቡ አልማዞች ትልቁ ነው።
99 ከመቶ የሚሆኑ የሐምራዊ ሮዛማ ቅይጥ ቀለም ያላቸው አልማዞች የካራት መጠን ከ10 በታች እንጂ 14 ካራት አይደርሱም።
ይህን አልማዝ ልዩ የሚያደርገውም መጠኑና የቀለም ስብጥሩ ነው ተብሏል።
ይህን ውድ አልማዝ በጨረታ አሸንፎ የገዛው ግለሰብ ማንነት ይፋ አልተደረገም።
ሐምራዊውን አልማዝ ለጨረታ ያቀረበው ግን የሩሲያ የማዕድን ኩባንያ አልሮሳ ነው።
"ዘ ስፕሪት ኦፍ ዘ ሮዝ" የተሰኘው ይህ ሐምራዊው አልማዝ ከድፍድፍ የአልማዝ ድንጋይ ነጥሮ የወጣው በሩሲያ በጎሮጎሳውያኑ 2017
ድፍድፍ አልማዙ ያን ጊዜ ሲወጣ ኒጂንስኪ የሚል የክብር ስም ተሰጥቶት ነበር። አልማዙ በዚህ ስም የተሰየመው የሩሲያ ፖሊሽ የባሌት ዳንስ ጥበበኛ ክብር ለመስጠት ነው። ቮስላቭ ኒጂንስኪ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ወደር ያልተገኘለት የባሌት ዳንሰኛ ነበር።
በዓለም ላይ እስከዛሬ ለፒንክ (ሮዝ) አልማዝ የተከፈለው ትልቁ ሽያጭ 71 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህም በ2017 በሆንግ ኮንግ በተደረገ ጨረታ የተሸጠው 59 ካራት አልማዝ ነው።
አልማዞች ብዙውን ጊዜ 150 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ውስጥ የኖሩና ወደላይኛው የምድር ክፍል በእሳተ ጎመራ አማካኝነት የወጡ ውድ የከበሩ ደንጋዮች ሲሆኑ እነዚህን ውድ የከበሩ ድንጋዮች ፈልጎ አግኝቶና አጽድቶ ለገበያ ለማቅረብ በአማካይ እስከ 20 ዓመት ሊወስድ ይችላል።
የተፈጥሮ አልማዝ እስከ 3 ቢሊዮን ዓመት ያህል እድሜ ያለው በብዙ የእሳት ጎመራና የመልከዓ ምድር ለውውጦች የተቀየጠ እንደሆነ ይታመናል። ከከበሩ ድነጋዮች ውስጥ እንደ አልመዝ ጠንካራ ማዕድን የለም።












