በኢንተርኔት አማካኝነት እጽ ይሸጡ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ እና የአሜሪካ ፖሊስ በጥምረት ባካሄዱት ኦፐሬሽን ማንነታቸውን በመደበቅ በኢንተርኔት አማካኝነት አደንዛዥ እጽ ሲሸጡ የነበሩ 179 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ተገለጸ።
ከግለሰቦቹ በተጨማሪ ፖሊስ ከ6.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያለው ጥሬ ገንዘብ እና ዲጂታል ገንዘብ የያዘ ሲሆን እጽ እና የጦር መሳሪያ ከግለሰቦቹ ጋር መያዙም ተነግሯል።
እነዚህ ሰዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከበርካታ የአውሮፓ አገራት እና አሜሪካ ሲሆን የተደራጁ ወንጀሎች ተከላካይ ኃይል ዩሮፖል፤ “ማንነትን በመደበቅ የሚደረገው ሕገ-ወጥ ግብይነት ጊዜው አብቅቷል” ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የዩሮፖል የኢንተርኔት ወንጀል ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ኤድቫራዳስ ሲሌሪስ “ድብቁ ኢንተርኔት ከአሁን በኋላ ሚስጥር አይሆንብንም” ብለዋል።
“ዲስራፕትቶር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ኦፕሬሽንን የአሜሪካው የፍትሕ ቢሮ እና ዩሮፖል በቅንጅት ያስፈጸሙት ሲሆን በኦፕሬሽኑ እንደ ፌንታኒ፣ ሄሮይን፣ ኮኬን እና ኤክስቴሲ የተሰኙ እጾች ተይዘዋል።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 179 ሰዎች መካከል 119 በአሜሪካ፣ 2 በካናዳ፣ 42 በጀርመን፣ 8 በኔዘርላንድ፣ 4 በዩኬ፣ 3 በኦስትሪያ እና 1 ግለሰብ ደግሞ ስዊድን ውስጥ መያዛቸው ተገልጿል።
ሰዎች ማንነታቸው እና መገኛቸው ሳይታወቅ ልዩ መተግበሪያዎችን በመጠቀም “ዳርክ ዌብ” ተብሎ በሚጠራው የኢንተርኔት ክፍል ላይ በርካታ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ያከናወናሉ።
“በዳርክ ዌብ” ላይ ሰዎች ማንነታቸውን መደበቅ ስለሚችሉ እንደ ኩላሊት ካሉ የሰው ልጆች አካላት እስከ አደንዛዥ እጽ መገበያየት ይቻላል ይላሉ የኢንፎሜሽን መረብ ደህንነት ባለሙያዎች።
ፖሊስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ወንጀለኞችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ ይገኛል። ኤድቫራዳስ ሲሌሪስ ሕግ አስከባሪ አካላት በቅንጅት መስራት ከቻሉ ወንጀለኞችን መቆጣጠር የማይቻልበት ምክንያት የለም ብለዋል።
እነዚህ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም “የዳርክ ዌብ ወርቃማ ዓመታት” እያለፉ መምጣታቸውን ያሳያል ተብሏል።












