ኮሮናቫይረስ፡ ለ15 ዓመት በወሲብ ንግድ ላይ የቆየችው ሴት ኮቪድ-19 ሕይወትን አክብዶብኛል ትላለች

ሩሐማ

ሩሐማ አበበ እባላለሁ። ትውልዴ ደቡብ ጎንደር አርብ ገበያ የሚባል ቦታ ነው።

*(ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟን ጨምሮ ማንነቷን ሊያሳውቁ የሚችሉ ነገሮች ተቀይረዋል ወይም እንዲቀሩ ተደርጓል።)

አርብ ገበያ ብወለድም አላደግኩበትም። አባቴ እኔ እንደተረገዝኩኝ ከእናቴ ጋር በመለያያቱ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። በስም ብቻ የማውቀው አባቴ በኋላ ላይ ህይወቱ እንዳለፈ ሰማሁ። እናቴ ደግሞ የሦስት ዓመት ልጅ ሆኜ ነው ህይወቷ ያለፈው።

ሰባት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ አያቴ ዘንድ እዚያው አርብ ገበያ ነው ያደግኩት።

በኋላ ላይ አክስቴ 'እኔ ላሳድጋት' ብላ ወደ ባህር ዳር ከተማ ይዛኝ መጣች።

ባህር ዳር በሁሉም ነገር የተሻለ ነበር። ትምህርቴንም ጀመርኩኝ።

አንደኛ ክፍል እያለሁ የደረሰብን ጉዳት ግን ህይወቴን እሰከወዲያኛው ለወጠው። እንጥሌ ወድቃ ጎሮሮዬ በማበጡ ምክንያት ወደ ሐኪም ቤት ይዘውኝ ሄዱ።

መርፌ የወጋኝ ሐኪም የሠከረ ይመስለኛል። ህጻን ስለሆነበርኩ በደንብ ባላስታውስም መርፌ ሲወጋኝ የአክስቴ ልጅ 'ኧረ ቸኮልክ' ስትለው ትዝ ይለኛል። አንዴ ሲወጋኝ ቀጭ ነው ያለው አጥንቴን ሲያገኘው። መርፌው ተሰብሮ የቀረ ይመስል አመመኝ።

የወጋኝ ቦታ ጎደጎደ። ሌላው ሰውነቴ ደግሞ አበጠ። ስራመድ እግሬን እየሳበኝ መሄድ ጀመረ። በአንድ ወሩ ቀኝ እግሬ አጠረ። እስከ አንድ ወር ድረስ በስርዓቱ እሄድ ነበር። መርፌ የተወጋሁበት ቦታ ጎድጉዶ ጣት ያስጋብል።

አሁን መኝታም ሲጎዳኝ ያመኛል። አሁንም መርፌው ተሰብሮ ቀርቷል ብዬ ነው የማስበው።

አሞኝ ይቀራል ብዬ በፍጹም አላስበኩም ነበር። ካበጠም በኋላ እግሬ እያጠረ መሬት መርገጥ አስቸገረኝ። በሁለተኛ ወሩ ወደ ሐኪም ቤቱ ስንሄድ ሐኪሙ የለም። እያዛለሁ ብሎ ሸሽቷል። ግማሹ አዲስ አበባ ሄዷል የሚል አለ። ሌሎች የት እንደሄደ አናውቅም አሉ።

በዚህ ምክንያት ራሴን አላጠፋም። እግሬን አልገዛውም። ምንም። ምን እላለሁ። [ረዥም ዝምታ]

በወቅቱ አንደኛ ክፍል እማር ነበር። ብቻ ብዙ ነገሮችን አጥቻለሁ። [ማልቀስ ጀመረች]። ቤተሰብ የለኝም ሁለተኛ ራሴን ሳጣ . . . [ከእንባዋ ጋር እየታገለች ቀጠለች]

ብዙም ሳትቆይ አክስቴ ሞተች። ከልጇ ጋር አብረን መኖር ጀመርን። እሷ ስታገባ ግን አማራጭ አጣሁ።

ሰው ራሱን ለማዳን ልመና ይቆማል። እኔ ግን አልመኘውም። የታክሲ እንኳን ሰው እንዲከፍልልኝ አልፈልግም።

ትምህርት ቤት አንዲት ጓደኛ ነበረችኝ። አበበች ትባላለች[ስሟ የተቀየረ]። አሁን አረብ ሃገር ነው ያለችው። ባህር ዳር ቀበሌ 5 ብትኖርም ሌላ ቦታ ነው ትውልዷ።

'ቤተሰብ አለሽ?' ስላት 'የለኝም' ትለኛለች።

ወዳጅነታችን ሳይጠነክር በፊት 'ቆሎ እሸጣለሁ' ትለኝ ነበር። 'በምሸጠው እኖራለሁ' ስትለኝ 'ቆሎ እየሸጥሽ እንዴት ያዋጣሻል?' ስላት ትስቅብኛለች [ፈገግ አለች]።

ሁሌም ትምህርት ቤት እያረፈደች ነው የምትገባው። አለቃ ይገርፋታል። 'ለምን ትተኛለሽ?' እላታለሁ። አንድ ቀን ግን 'ብዙ ነገር አለ። ስንወጣ እናወራለን' አለችችኝ።

ከትምህርት ቤት ስንወጣ 'ምን ነበር አወራሻለሁ ያልሽኝ?' ስላት። 'እንደዚህ እንደዚህ ነው የምሰራው' አለችኝ። 'ከወንድ ጋር እወጣለሁ። ከብዙ ሰዎች ጋር' አለችኝ። ብዙ ነገር ነገረችኝ። አለቀስኩ።

'ሩሐማ ቤተሰብ ይሄን እንደምሰራ አያውቅም' አለችኝ። መጀመሪያ ላይ 'እንዴት? የሚያውቅሽ ወይም መምህርሽ ቢመጣስ?' ስላት 'ላይለየኝ' ይችላል አለችኝ። 'መብራቱ ቀይ አምፖል ነው' ብላ አሳየችኝ ቤቱን ወስዳ። ማታ ላይ ከቤት አድረን አይቼዋለሁ። ቀይ ቀለም በተቀባው አምፖል በቀላሉ እንደማትለይ እኔ እንኳን ቤቷ ድረስ ሄጄ አይቼዋለው። 'እኔ መሆኔን ሳያውቅ አንድ ጊዜ አብሮን የሚማር ልጅ ጠይቆኝ ያውቃል' አለችኝ።

በወቅቱ ጥልፍ እየሠራሁ ነበር የምተዳደረው።

የምሠራው ጥልፍም ሳጣ አወያያታለሁ። 'ነይ እኛ ጋር ነገ ሌላ ሰው እንሆናለን። ቀን ሲያልፍ ሌላ ቦታ ሄደን እንኖራለን' ትለኛለች። 'እኔ ቀን ቢወጣልኝም አልተውሽም' ትለኛለች።

በኋላ አንድ ክፍል ቤት 30 ብር ተከራየችልኝ። አልጋ እና አንዳንድ ዕቃዎችን አሟላችልኝ።

Short presentational grey line

የመጀመሪያ ቀን ምሽት አንድ ትልቅ ሰው መጣ። 'ለስብሰባ ነው ከአዲስ አበባ የመጣሁት' አለኝ። ሁኔታዬን አየና 'ለምን ወደ ሥራው ገባሽ?' ሲለኝ ነገርኩትና አዘነ። 'ቤቱን ስንት ተከራየሽ?' ሲለኝ '30 ብር' አልኩት። ማደር ቢፈልግም ሂድ አልኩት።

'ልትሠሪ አይደለም?' አለኝ። ጓደኛዬን ጠራትና አናገራት። 'ውጣ አለችኝ' አላት።

እሷ 'ልትሠሪ አይደል አንዴ?' አለችኝ። ለሊቱንም ሙሉ 'ይህ ህይወት ላንቺ አይደለም' እያለ ሲያወራኝ አደረ። 'ሌላ ሥራ' አለኝ። ምንም ሳናደርግ አደርን። 'በዚህ ህይወትሽና በዚህ ፍርሃትሽ በሽታም አለ' አለኝ። ጓደኛዬ እንኳን ያልነገረችኝን ብዙ ነገር ነገረኝ። ስለኤድስ አንኳን እውቀቱ አልነበረኝም።

ሲሄድ ስልክ ስላልነበረኝ የተከራየሁበትን ቤት ስልክ ሰጠሁት። መጀመሪያ ሦስት ሺህ ብር፤ ቀጥሎ ሁለት ሺህ ብር ከዚያም 1500 ብር ላከልኝ። ቤት በመቀየሬ እና የሰውየው ስልክ ስላልነበረኝ በኋላ ላይ ግንኙነታችን ተቋረጠ።

ወደ ወሲብ ንግድ የገባሁት የ15 ዓመት ልጅ ሆኜ ነው። አሁን 30 ዓመቴ ነው። 15 ዓመታት በዚህ ሥራ አሳለፍኩ ማለት ነው። እየሠራሁም ትምህርቴን እከታተል ነበር። ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የተማርኩት እየሠራሁ ነው።

የመጀመሪያ ቀን ያደርኩት ከፖሊስ ጋር ነው። አንገራግሮኝ ነው ያደረው። ገንዘብ እንኳን አልከፈለኝም።

አዲስ መሆኔ ገብቶታል። ከባልደረቦቹ ጋር ሲዞር ቆይቶ ተመልሶ መጣ። መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር። መጥቶ 'ላድር ነው' ሲል 'አይቻልም' ስለው አንገራገረኝ። ገንዘብም አልጠየኩትም። እንዴት እንደሚጠየቅም አለውቅም። አሁን ለራሴ ሳይሆን ሌላም አስተምራለሁ።

አደረና ጠዋት 'ማታ እመጣለሁ እሺ' ብሎኝ እንደ ባል ወጥቶ ሄደ።

ለጓደኛዬ 'ያደረው ሰውዬ ማታ እመጣለሁ ብሎ ሳይከፍለኝ ሄደ' ስላት፣ ሳቀችና ከአሁን በኋላ ገንዘብ ቀድመሽ ተቀበይ አለችኝ።

የመጀመሪያውን ቀን ሳስበው ይዘገነንነኛል። አንዳንዴ ምን ቀን ነበር እላለሁ። እንደዚያ ከሆነ በኋላ ከሥራው ብወጣ እል ነበር።

ሆኖም የተሻለ ሰው ሲመጣ መላመድ ይመጣል። ልውጣ ስል ደግሞ የገቢ ጥያቄ ይመጣል። ገንዘብ እያገኘሁ አይደለም በሚል መላመድም አለ። አሁን ከመላመድ እንደ ቤተሰብ ነኝ። ግን ከባድ እና ከባድ ሸክም እንደዚህ ሥራ የሚከብድ የለም።

ተነጋግረው ገብተው ገንዘብን አብልጠው ገንዘብ ልጨምርና ያለምንም ኮንዶም ልጠቀም የሚሉ አሉ። ሰውን በገንዘብ እንደሚገዙ። ገንዘብ የነገር ማስፈጸሚያ ነው። ማመኚያ የሚያደርጉት አሉ። እነሱ በገንዘብ አምነው አንተን ጥለው በገንዘብ ቀይረው ሊገዙ ይፈልጋሉ።

የተለያየ ነገር መሥራት እችላለሁ ብዬ ጓደኛዬ ጋር ልብስ ስፌት ተለማመድኩ። ጥልፍም እችላለሁ። ግን የስፌት መኪናውን መግዛት አልቻልኩም። ገንዘቡ አይጠራቀምም።

የቤት ኪራይ ሁለት ሺህ ብር ነው። የቤት ኪራይ ቅድሚያ እከፍላለሁ። ብዙ ወጪ አለ። እየሰለቸኝም ዛሬ ካገኘሁ ሁለት ወይም ሦስት ቀን እተኛለሁ።

አንዱ ጠጥቶ ይመጣል። ሰክሮ፣ ቅሞና መርቅኖ ይመጣል። እኔን በገንዘብ ሊገዛ ይፈልጋል። እናም በጣም ከባድ ነው። ለመናገርም ከባድ ነው። የተለያየ ነገር ይጠይቅሃል።

ዛሬ ከሠራሁ ካገኘሁ ሁለት ወይም ሦስት ቀን እተኛለሁ። ዛሬ 300 ብር ባገኝ ነገም ላገኝ እችላለሁ። በ100 ተጠቅሜ ሌላውን መቆጠብ እችላለሁ። ግን መሥራት ስለማልፈልግ በቀጣይ ቀናት አልሠራም። [ወሲብ] ከባልም ጋር ቢሆን እንኳን ሁልጊዜ የሚደብር ይመስለኛል። ሰው ወዶት አይደለም ወደዚህ ህይወት የሚገባው።

አካል ጉዳተኛ መሆኔ ደግሞ ሌላ ተጽዕኖ ይፈጥራል። አንዳንዱ አብሮኝ ለማደር ሊጠይቀኝ ፈልጎ ተመልሶ ይሄዳል።

'እንዳይሰማሽ' የሚሉም ብዙ ሰዎች አሉ። 'አንቺ ለምን እንደዚህ ትሠሪያለሽ?' የሚሉኝም አሉ።

ሥራው አስጠላኝ። መጀመሪያ ላይ ሁሉ ነገር ሲምታታብኝ ኮብልስቶን እሠራ ነበር። ኮብልስቶን ሰልጥኜ ተቀጥሬ እየሠራሁ ነበር። ሥራው ድንጋይ መፍለጥም ቢሆን ማህበሩ ሲበታተን አቆመ።

ዞሬ ቀጠልኩበት። አንድ ቀን ኮብልስቶን አብሮኝ ሲሠራ የነበረ ልጅ ግብት አለና አይቶኝ አማተበና ምንም ሳይለኝ ዞሮ ሄደ።

ሌላ ቀን ደውሎ ሰደበኝ። 'ለምን ትሠሪያለሽ? ሲለኝ 'ሃብታም ስለሆንኩ ነው' አልኩት። አሁንም አልፎ አልፎ እየደወለ 'አልወጣሽም? በናትሽ ውጪ' ሲለኝ 'አንተ ሁለት መኪና አለህ። አንዷን ሽጥና ገንዘቡን ስጠኝ ልሥራበት' እለዋለሁ። ይስቃል። ብዙ ነገር ይከብዳል ብቻ።

Presentational grey line

ብዙ ገጠመኝ ይገጥማል። አንዱ አካል ጉዳተኛ መሆኔን አላወቀም። መጽሐፍ እያነበብኩ ገባ። ተነጋገረን። ቤቷ ጠባብ ነች። አልጋ አነጣጥፌ ተኛን። ከተኛን በኋላ የሆነ ነገር ሲፈልግ ልሰጠው ስል 'እንዴ ምን ማለት ነው?' አለ። 'አካል ጉዳተኛ ነሽ እንዴ?' አለ። 'አዎ' ስለው ልብሱን ለበሰና 'ገንዘቤን' አለ። 'ለምን እሰጥሃለሁ? ጊዜ አቃጥለሃል። ሥራ ልሰራ ነው የተቀመጥኩት። ደልቶኝ ወይም ሞልቶኝ አይደለም' አልኩት። 'ምን ልትሠሪ ተቀመጥሽ?' ሲለኝ 'ያንተን ጸጉር ላበጥር' አልኩት።

ካልሆነ 'ሂድ' ስለው 'ለምን ጉዳተኛ ነኝ አላልሽኝም?' አለ። 'እንደውም ፖሊስ ጥሪ' አለኝ።

ጠራሁና ፖሊስ መጣ ብሬን ሳልይዝ ከቤት አልወጣም አለ። ጃኬቱ አልጋ ላይ ነበር። ፖሊስ ጣቢያ ሄድን። ተቀመጠን ፖሊሱ 'ብር መልሺ ነው የምትላት" ሲለው 'አዎ' አለ። 'ብር ብትመለስልህ ይዘህ ትሄዳለህ?' ሲለው 'አዎ' አለ።

'መታወቂያህን አሳየኝ?' አለው። ከጃኬቱ ኪስ ሊያውጣ ከትከሻው ላይ ጃኬቱን ሲያወርድ ለካ ጃኬቱ መስሎት ትከሻው ላይ ጣል አድርጎት ከእኔ ቤት የወጣው የራሴን ፒጃማ ነበር [ሳቀች]።

ውርድ አድርጎ ሴያየው ፒጃማ ነው። አፈረ ምን ይበል። 'ብሩንም አልፈልግም እሄዳለሁ' ሲል ፖሊሱ በነገሩ ሳቀ። 'መታወቂያህን ካላሳየሀኝ አትሄድም' ሲለው 'አንዴ ከተነቃ ይታለፋል' አለ። ጃኬቱ ከቤት ቀርቷል። ፒጃማውን ሰጠኝ ብሩን ተወልኝ። ጃኬቱን በነገታው ወሰደ። ብቻ የጠጣ ሰው ትክክል አይደለም።

አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ኮሮና መጣ።

ኮሮና በጣም አስከፊ እና አሰቃቂ ነው። ለኤድስ ኮንዶም እጠቀማለሁ። ባለፉት ሰባት ዓመታት በየሦስት ወሩ እመረመራለሁ። ኮሮና ግን ከባድ ነው። ልሥራ ካልኩን ለበሽታው መጋለጥ ይኖራል። አይ ይቅርብኝ ብዬ እንዳልቀመጥ በረሃብ ልሞት ነው።

ብዙ ባይሆንም አሁንም እየሠራሁ ነው። ኮሮኖ ሰውና ሰው አያገናኝም። አብሮ ለመተኛት እንደ ኮንዶም ዓይነት የምንጠቀመው ነገር የለም።

ከተከራየንባቸው ሰዎችም እየለየን ነው። እኛ የቀዳንበትን ቧንቧ እያጠቡት ነው የሚጠቀሙበት። ምክንያቱም እኛ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስለምንገናኝ 'እነሱ ከነኩት ዝም ብላችሁ አትንኩት' እየተባለ ከሰው የተገለለንበት ሰዓት ነው።

ለኤች አይቪ ኮንዶም አለ። ለዚህ [ለኮሮና] ምንም የለም። ከሰው ነጥሎን በሬን ዘግቼ እውላለሁ። ከሰው አያገናኝም።

በሽታው እንደመጣ ኮሮና ኮሮና ሲባል አንደ ሰው መጣ ማስክ (የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል) አድርጌ ስለነበር 'ምንድነው አለኝ?'። 'ባህር ዳር አይደለም የምትኖረው? የሚወራውን አትሰማም?' አልኩት። 'አላወቅኩም ሌላ ነገር ልናደርግ ነው አይደል?' አለኝ።

ውሃ አቀረብኩ 'ታጠብ ሳኒታይዘርም አለ ተጠቀም' አልኩት። 'አብሬሽ ልተኛ እያልኩ ነው። ካላወለቅሽው አልተኛም 'አለ። ብሩን ስለፈለግኩኝ 'አበድሩኝ' እና 'ስጡኝ' ብሎ ከመለመን እጄን ታጠብኩ ሳኒታይዘር እኔም እሱም ተጠቀምን። ተኛን። ፊቴን ዞሬ ተኛሁ። ግማሽ ለሊት ላይ 'አንቺን ፈልጌ እንጂ ዞረሽ ከተኛሽስ ልሂድ' ሲል 'እሺ ሂድ' ብዬ የሰጠኝን ብር ሰጠሁት። ወጥቶ ሄደ።

ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ እየሳለ ገባ። ገብቶ ሲስል ሸሸሁት። 'ምን ፈልገህ ነው?' ስለው 'ፈራሽኝ እንዴ?' አለ። 'እያሰላክ ነው' እኮ ነው አልኩት። ያስነጥሳል፤ ያስላል። ወጥቶ ሄደ።

'[የጓደኛዋን ስም ጠቅሳ] አንቺ' አልኳት። 'እኔም ጋር መጥቶ ሲያስለው ውጣ አልኩት' አለች።

ሰውየው ተመለሰና 'ኮሮና አንቺን እንጂ እኔን አይዘኝም' አለ።

በቀላሉ የሚለይበት ምልከት የለውም። ኤድስ ማለት ነው። ምልክት ወይም ቁስል ቢሆን እሸሻለሁ። እያስነጠሰ ግን አላስገባውም።

ሁሌም ማስክ እጠቀማለሁ። ግን ብዙዎች 'ለምን ትጠቀሚያለሽ?' ይላሉ። እኔ ከቤት ወጥቼ ስሄድም ሁሌም እጠቀማለሁ። ማንንም በእጄ አልነካም።

ደንበኞች አሉኝ። ግን በኮሮና ምክንያት አይመጡም። ብዙ ሰው ራሱን ይፈልገዋል።

አሁን ምንም አንሠራም። በወር 400 ብሠራ ጥሩ ነው። አንድ ጓደኛዬ ካላት እሷ ጋር ምሳ በልቼ ቡና ጠጥቼ ልውል እችላለሁ። እሷም እኔ ዘንድ።

ቤት ኪራይ ምናምን እያሉ የአካባቢው ወጣቶችም እየሰበሰቡ ካለው እያዋጡ የአንድ ወር የቤት ኪራይ ከፍለውልናል።

የምሠራው ነገር ባገኝ ከዚህ ህይወት እወጣ ነበር። ብዙ ነገር አስብ ነበር። ተቀማጭ ቢኖረኝ እቁብ ገብቼ እንደዚህ ባደርግ እላለሁ።

ዕቁብ እንዳልገባ ማህበረሰቡ በየራሱ ጭንቅ ላይ ነው። ያላቸው ጋር ደግሞ እንዳልገባ ደግሞ ማን ዋስ ይሆነኛል። 'በልታ እልም ብትልስ?' ይላሉ። ወር ደሞዝተኞች አሉ፤ ከእነሱ ጋር ልግባ ለማለት ደግሞ ያላቅም መንጥጠል ነው። የሚያበረታታም የለም።

ኮሮና
Banner