ታዳጊዎችን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ተከሶ የነበረው ቱጃሩ ጄፈሪ ኤፕስተን አሟሟት ጥያቄን ፈጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሰሞኑ በእስር ቤት ራሱን ያጠፋው ቱጃሩ አሜሪካዊ ሞት ጥያቄዎችን እያስነሳ ነነው። ቢሊየነሩ ጄፈሪ ኤፕስተን ህፃናትን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ክስ እስር ቤት ነበር።
አስከሬኑ የተገኘው ቅዳሜ እለት ኒውዮርክ በሚገኘውና ከፍተኛ ቁጥጥር ባለበት ማረሚያ ቤት ነው።
ግለሰቡ ባለፈው ወርም የዋስ መብቱን ሲከለከል ራሱን ስቶ የተገኘ ሲሆን ራሱንም ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ ነበር ተብሏል።
በአሁኑ ወቅትም ጥያቄዎችን እያጫረ ያለው ጉዳይም ራሱን የማጥፋት ሙከራውን ተከትሎ ጥብቅ ክትትል ለምን አልተደረገለትም የሚለው ጉዳይ ነው።
የኒውዮርኩ ከንቲባ ቢል ደ ብላሲዮ ጉዳዩ በቀላሉ መታየት እንደሌለበትና በአሟሟቱ ላይ ምርምራ መደረግ እንዳለበት አበክረው ተናግረዋል።
"ሁላችንም ማወቅ የምንፈልገው ጉዳይ ቢኖር፣ ምን ያውቅ ነበር የሚለውን ነው" ለሃገሪቱ ፕሬዚዳንትነት እየተወዳደሩ ያሉት ከንቲባ አክለውም "የትኞቹ ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች ናቸው በዚህ ህገወጥ ተግባር የተሳተፉት? ይህ መረጃ ከጄፈሪ ኤፕስተን ጋር አብሮ መቀበር የለበትም። አብረውት የተሳተፉትም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ምርምራ ያስፈልጋቸዋል። "
ባለፈው ወር ህፃናትን በወሲብ ንግድ በማሰማራት ወንጀል ተከሶ የነበረው ቢሊየነሩ የዋስ መብቱን ተከልክሎ ነበር።
ከጥቂት ቀናትም በፊት ቢሊየነሩንና ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችን በተመለከተ አዲስ መረጃ በፍርድ ቤት መውጣቱን ተከትሎ የግለሰቡ መሞት አጋጣሚ ነው የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሪፐብሊካኑ ሴናተር ቤን ሳሴ በበኩላቸው ለጠቅላይ አቃቤ ህግ በፃፉት ደብዳቤ "የፍትህ ክፍሉ ሞቱን መከላከል ሲቻል እሱን ማድረግ ተስኖታል፤ የሱን ሞት ተከትሎም ከጄፈሪ ኤፕስተን ጋር ተመሳጥረው ይህንን ህገ ወጥ ተግባር ሲያከናውኑ የነበሩ ግለሰቦች ቀን የወጣላቸው መስሏቸዋል" ብሏል።
"ከማረሚያ ቤቱ ጠባቂ ጀምሮ በተለያዩ የፍትህ ክፍል ያሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ግለሰቡ ራሱን ሊያጠፋ እንደሚችል ያውቁ ነበር። አሁንም ቢሆን የሚያውቀው ሚስጥር አብሮ መቀበር የለበትም " ይላል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች አሉ፤ ምላሽም ማግኘት አለባቸው፤" አክለውም "የኤፕስተን ሞት መስማት በጣም ያበሳጫል፤ የራሳችንም ምርመራ ጀምረናል" ብለዋል።
በጄፈሪ ኤፕስተን ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባሉ ግለሰቦች በበኩላቸው ቢሊየነሩ የመጨረሻ ፍርድ ሳያገኝ መሞቱ እንዳሳዘናቸው ነው።
"በጣም ተናድጃለሁ፣ተጎድቻለሁ ምክንያቱም አሁንም ቢሆን ጥቃት ከደረሰብን ግለሰቦች በላይ መሆኑን ለማሳየት ቀላሉን መንገድ መርጧል" በማለት የጥቃቱ ሰለባ ከተባለችው አንዷ ጄና ሊዛ ጆንስ በመግለጫዋ አትታለች።
"ከጥቃቱ ያመለጡ ግለሰቦችን በፍርድ ቤቱ እንደማያገኝ ስረዳ በጣም አዝኛለሁ" በማለት ሌላ ከጥቃቱ አመለጠች የተባለችው ጄኒፈር አራኦዝ ለሲኤንቢሲ ተናግራለች።
አክላም "ባደረገው ድርጊት ጠባሳውን ተሸክመን እስከ ህይወታችን መጨረሻ እንኖራለን"ብላለች።
ጥቃቱ ደረሰባቸው የተባሉ ታዳጊዎች ጠበቃ ሊዛ በከኩሏ ጥቃቱ የደረሰባቸው ግለሰቦች ላይ የማይሽር ጠባሳ ትቶ በማለፉ አሁንም ቢሆን ፍትህን ለደንበኞቿ እንደምትሻና ካሳንም እንደምትጠይቅ በትዊተር ገጿ አስፍራለች።
በኒውዮርክ አቃቤ ህግ የሆኑት ጆፈሪ በርማን በበኩላቸው የጄፈሪ ኤፕስተንን ሞት "የሚረብሽ" ብለውታል። ጥቃቱ ደረሰባቸው ለተባሉትም ምርመራው እንደሚቀጥልና ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል።
የጄፈሪ ኤፕስተን ክስ ምን ነበር?
ጄፈሪ ኤፕስተን አስራ ስምንት አመት ያልሞላቸውን ታዳጊ ልጃገረዶች እንደ ጎርጎጎሳውያኑ አቆጣጠር 2002-2005 በማንሃተንና ፍሎሪዳ በሚገኘው ቤቱ እየከፈለ በወሲብ ንግድ አሰማርቷቸዋል የሚል ነው።
በግል አውሮፕላኑ ኒውጀርሲ ሲያርፍ ባለፈው ወር በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ ከአስራ አንድ አመት በፊትም አነጋጋሪ በተባለው ሚስጥራዊ ስምምነት ጥፋተኛ መሆኑንም አምኖ ክሱን ማስቀረት ችሏል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ ምስጢራዊ ስምምነት በቅርቡ አነጋጋሪ ሆኖ የነበረ ሲሆን ባለፈው ወርም በዚህ የተነሳ የቀድሞው ጠቅላይ አቃቤ ህግ አሌክስ አኮስታ በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ለቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አቃቤ ህግጋት ጄፈሪ ኤፕስቴይን ጥቃቱ ለደረሰባቸው ሁለት ግለሰቦች ችሎት እንዳይቀርቡ ለማባበል ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በመክፈል ወንጅለዋቸዋል።
ጀፈሪ ኤፕሰትን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ 45 አመታት እስር ይጠብቀው ነበር።
ጄፈሪ ኤፐስተን ማን ነው?
ኒውዮርክ የተወለደው ጄፈሪ ኤፕስተን ወደ ንግዱ አለም ከመቀላለሉ በፊት መምህር ነበር።
ከቀረበበት የወንጀል ክስ በተጨማሪ ከቱጃሮችና ባለስልጣናት ጋር ባለው ግንኙነት ይታወቃል።
ከነዚህም መካከል የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንና የእንግሊዙ ልዑል አንድሪው ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎችም ይታያል ተብሏል።
በጎርጎሳውያኑ 2002ም ዶናልድ ትራምፕ ለአስራ አምስት አመታት ጓደኛቸው እንደሆነና "አስደናቂ ሰው ነው፤ እንደኔ ቆንጆ ሴቶችን ይወዳል፤ እሱ እንዳውም በእድሜ አነስ ያሉትን" እንዳሉ ኒውዮርክ ማጋዚን (መፅሄት) አስነብቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ባለፈው ወር ፕሬዚዳንቱ ቃላቸውን አጥፈው የጄፈሪ አድናቂ እንዳልሆኑና ከአስር አመታትም በላይ አውርተው እንደማያቁ ተናግረዋል።
በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2006 ጄፈሪ ኤፕስተን ከ18 አመት በታች ከሆነች ታዳጊ ጋር ገንዘብ በመክፈል ወሲብ በመፈፀም ተከሰው የነበረ ሲሆን ጉዳዩም ወደ ኤፍቢአይ ተመርቶ ነበር።
ነገር ግን በአመቱ በጊዜው ከነበረው የጠቅላይ አቃቤ ህግ አሌክስ አኮስታ ጋር ሚስጢራዊ የተባለውን ስምምነት በመፈፀመም አምኖ ሳይከሰስ ቀርቷል።
በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2008 ለአስራ ሶስት ወራት እስር የተፈረደበት ቢሆንም፤ በሳምንት ስድስት ቀን፤ በቀን አስራ ሁለት ሰአታት ስራ እንዲሄድ ተወስኖ ነበር።













