የጣልያኑ ምክትል ጠ/ሚ እና የሆሊውዱ ተዋናይ በስደተኞች ጉዳዩ ተጋጭተዋል

የሆሊውዱ ተዋናይ ሪቻርድ ጌሪ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሪቻርድ ጊር፤ የጣልያኑ ጠቅላይ ምክትል ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒን ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አመሳስሎ ሲታቸቸው ተሰምቷል

የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሆሊውዱ ተዋናይ ሪቻርድ ጊር በስደተኞች ምክንያት ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

ተዋናዩ ሪቻርድ ጊር የጣልያን መንግሥት ሜድትራኒያን ባሕር ላይ አንዲት መርከብ ውስጥ ታሽገው የሚገኙ ስደተኞችን ጉዳይ አንድ እንዲለው አሳስቧል።

160 ስደተኞች፤ አንዲት የስፔን የእርዳታ መርከብ ውስጥ እንዳሉ ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ከአንድ ሳምንት በላይ እንዳስቆጠሩ መነገር ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።

የጣልያን መንግሥት 'ሰዎችን ከሰው በታች ማየት ማቆም አለበት' ሲል ነው ተዋናዩ ወቀሳውን ያሰማው። ተዋናዩ በጣልያን መንግሥት መልሕቅ መጣያ የተከለከለችውን መርከብ ሄዶ መጎብኘት ችሏል።

የጣልያኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ፤ ተዋናዩ ካሻው ስደተኞቹን ወደ ሆሊውድ ይዟቸው ሊሄድ ይችላል ሲል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሪቻርድ ጊር፤ ስደተኞች ወደሃገራቸው እንዳይገቡ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት የጣልያኑ ጠቅላይ ምክትል ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒን ከአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር አመሳስሎ ሲተቻቸው ተሰምቷል።

የጣልያኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የጣልያኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ

«ይህ ስደተኞችን ከሰው በታች አድርጎ የማየት ጉዳይ መቆም አለበት። ደሞ ይቁም የምንል ከሆነ መቆሙ አይቀርም» ሲል ነው የሆሊውዱ ሰው ድጋፉን ለስደተኞች የሰጠው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ለመስጠት ብዙም አልዘገዩም። «ይህ ለጋስ ሚሊዬነር ለስደተኞች ድጋፍ ማድረጉ እንዳው የሚያስመሰግነው ነው። ቢቻለው 160ዎቹን ስደተኞች በግል አውሮፕላኑ ወደ ሆሊውድ ወስዶ በልጥጥ መኖሪያ ቤቱ ቢያኖራቸው ደግሞ እጅግ መልካም ነው። እናመሰግንሃለን ሪቻርድ!»

ሳልቪኒ ስደተኞችን ይዘው ወደ ጣልያን ወደብ የሚመጡ የእርዳታ መርከቦች ላይ እገዳ እንዲጣል ከጊዜ ጊዜ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።