ለትራምፕ አደገኛ መርዝ በፖስታ የላከችው ፍርድ ቤት ቀረበች

ፓስካል ፌሪዬር

የፎቶው ባለመብት, HIDALGO COUNTY SHERIFF'S OFFICE

ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ራይሲን የተባለ ገዳይ መርዝ በፖስታ አሽጋ ልካለች የተባለችው ካናዳዊት ሴት በአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት ክስ ቀረበባት።

ነዋሪነቷን በካናዳ የሆነው ፓስካል ፌሪዬር የተባለችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር የዋለችው ባሳለፍነው ዕሁድ በኒው ዮርክ ቡፋሎ በኩል አድርጋ ወደ አሜሪካ ልትገባ ስትል እንደሆነ ተገልጿል።

ባለስልጣናት እንዳሉትም ተጠርጠሪዋ በወቅቱ ሽጉጥ ይዛ ነበር።

ፍርድ ቤት ከቀረበች በኋላ ምንም ጥፋት አልሰራሁም፤ ፕሬዝዳንቱ ላይም የግድያ ዛቻ አልፈጸምኩም በማለት ተከራክራለች።

ባሳለፍነው ሳምንት ይችው ግለሰብ ልካዋለች የተባለው በገዳይ መርዝ የተሞላ ፖስታ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሚነኖሩበት ዋይት ሃውስ ከመድረሱ በፊት ነው የተገኘው።

በደብዳቤውም ላይ ተጠርጣሪዋ ዶናልድ ትራምፕ ከመጪው ምርጫ እራሳቸውን እንዲያገሉ ጠይቃለች። በደብዳቤ ማሸጊያ ውስጥም ራይሲን የተባለ ገዳይ መርዝ መገኘቱም ተገልጿል።

''ክቡር ፕሬዝዳንት አዲስ ስም አውጥቼልዎታለው፤ 'አስቀያሚው ጨካኝ አሻንጉሊት' '' ስትል በደብዳቤዋ ገልጻለች ብሏል የአሜሪካው ፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ።

''ያወጠሁልዎትን ስም እንደሚወዱት ተስፋ አደርጋለሁ። አሜሪካን እያመሰቃቀሏት ነው፤ አሜሪካውያንምም ወደ ምስቅልቅል ህይወት እየመሩ ነው። አሜሪካውያን ዘመዶች አሉኝ፤ እናም ቀጣዮቹ አራት ዓመታት በእርስዎ ፕሬዝዳንትነት እንዲያልፉ አልሻም። እርግፍ አድርገው ይተዉትና ከምርጫው ውድድር እራስዎን ያግልሉ'' ይላል ደብዳቤው።

ኤፍቢአይ እንዳስታወቀው በደብዳቤው ላይ የተጠርጠሪዋን የጣት አሻራ ያገኘ ሲሆን በዚህ የማብቃት ሀሳብ አልንበራትም ብሏል። በደብዳቤዋ ላይ መርዙ ካልተሳካላት በቀጣይ ስለምትወስደውም እርምጃ ጽፋለች ብሏል።

አደገኛ መርዙን ልዩ ስጦታ በማለት ከገለጸችው በኋላ ''መርዙ የማይሰራ ከሆነ በደብን ጠንከር ያለ ሌላ መርዝ ሰርቼ እልክልዎታለሁ። ካልሆንም ደግሞ መምጣት ስችል በሽጉጤ እገድልዎታለው'' ብላለች።

ኤፍቢአይ አክሎ እንዳስታወቀውም ተጠርጣሪዋ ከዋይት ሀውስ በተጨማሪ በሌሎች አምስት አድራሻዎች ራይሲን የተባለውን መርዝ ሳትልክ አልቀረችም። ከእነዚህም መካከል አንድ ማረሚያ ቤትና የፖሊስ ኃላፊ ቢሮ ይገኝበታል።

ተጠርጣሪዋ ትናንት ማክሰኞ ከሰአት ቡፋሎ ኒው ዮርክ ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን በወቅቱም የፈረንሳይኛ አስተርጓሚ አብሯት እንደነበር የአካባቢው መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

በፍርድ ሂደቱም ፓስካል ፌሪዬር ፍርድ ቤቱ ጠበቃ እንዲያቆምላት ጠይቃለች።

ፍርድ ቤቱም ቀጣይ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ለመስከረም 28 ቀጠሮ ይዟል።

ተጠርጣሪዋ ከአገር ልትሰወር ስለምትችልም የቀጠሮ ቀኗ እስከሚደርስ በዩኤስ ማርሻልስ ቁጥጥር ስር ትሆናለች ብለዋል ኃላፊዎች።