ስልክዎ ውስጥ ያለው ወርቅ ለእጽ አዘዋዋሪዎች ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ያውቃሉ?

ወርቅ

አንድ ወርቅ የሚያጣራ ድርጅት ወንጀለኞች ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲያስገቡ መንገድ ያመቻቻል። ይህ ድርጅት ለተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ለመኪና ሥራ የሚውል ወርቅ ለገበያ አቅርቧል።

ካሎቲ የተባለው ድርጅት መቀመጫው ዱባይ ነው። ወርቅ ከወንጀለኞች ይሸምታል።

ከስድስት ዓመት በፊት ድርጅቱ ሕገ ወጥ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ በማስገባት ቀንደኛ መሆኑን ለዓለም እንዲያስጠነቅቅ ለአሜሪካ ግምዣ ቤት ተገልጾ ነበር።

ማስጠንቀቂያው ግን አልተሰጠም።

ካሎቲ ለምርቶቻቸው ውድ ማዕድን ለሚጠቀሙት አፕል፣ አማዞን እና ጀነራል ሞተርስ ወርቅ ሸጧል። ይህ ማለት እነዚህ ተቋሞችና ሸማቾች በተዘዋዋሪ ለወንጀል እንቅስቃሴ ድጋፍ አድርገዋል ማለት ነው።

የካሎቲ ወኪሎች ወንጀል ወይም ሕገ ወጥ ክንውንን ሆነ ብለን አልደገፍንም ብለዋል።

ካሎቲ ያደረገው ምንድን ነው?

ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ቡድን እንዲሁም ቢቢሲም ያገኟቸው ሚስጥራዊ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፤ የአሜሪካ ግምዣ ቤት እአአ 2014 ላይ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ተጠይቆ ነበር። መረጃውን ያቀበሉት ለሦስት ዓመታት ጉዳዩን ያጣሩ መርማሪዎች ነበሩ።

‘ሀኒ ባጀር’ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ምርመራ የተካሄደው በአሜሪካው የጸረ አደንዛዥ እጽ ተቋም (ዲኢኤ) ነው።

ካሎቲ ወርቅን ተጠቅሞ በርካታ ሕገ ወጥ ገንዘብ አዘዋውሯል፤ አስተላልፏልም።

በየትኛውም አገር ያሉ ወንጀለኞች ከእጽ ዝውውር ወይም በሌላ መንገድ በተገኝ ገንዘብ ቅንጥብጣቢ ወርቅ ወይም ጌጣ ጌጥ ገዝተው ለካሎቲ እንደሚሰጡ ሰነዶች ይጠቁማሉ።

ካሎቲ ደግሞ ለወርቁ ምላሽ በርካታ ገንዘብ ይሰጣቸዋል። ወይም ያስተላልፍላቸዋል።

የአሜሪካ ግምዣ ቤት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ ተነግሮት ምንም እርምጃ ያልወሰደው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ላለማስቀየም ነው።

ካሎቲ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ በመርማሪዎች ስላልተጠየቀ ያለው ነገር የለም። የአሜሪካ ግምዣ ቤትም ምንም አላለም።

በመላው ዓለም ካሎቲ ገንዘብ ባስቀመጠባቸው ባንኮች አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ምርመራው ያሳያል። የአሜሪካ መንግሥት ይህን ምርመራ ለሕዝብ ይፋ አላደረገም።

ደችስ ባንክ፣ ባርክሌስ እና ሌሎችም 34 ባንኮች ስለ ካሎቲ ለአሜሪካ ግምዣ ቤት ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ወንጀሎች ክፍል ሪፖርት አስገብተዋል።

በሪፖርቱ መሠረት፤ ከ2007 እስከ 2015 ድረስ 9.3 ቢሊዮን ዶላር ዝውውር ተደርጓል።

2017 ላይ ሕገ ወጥ ገንዘብን በሕጋዊ መስመር የሚያስገባ ቡድን ፈረንሳይ ውስጥ ተከሷል። በአውሮፓ አደንዛዥ እጽ ያሰራጭ ነበር።

ይህ ቡድን የሚቆጣጠረው ረንዴ ኢንተርናሽናል ለካሎቲ 146 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ መሸጡን ቢቢሲ ከወራት በፊት ደርሶበት ነበር።

ካሎቲ ሕግ ወጥ ተግባር እንዳልፈጸመና በአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳልተከሰሰ ይናገራል።

የድርጅቱ ጠበቆች እንደሚሉት፤ በየዓመቱ የሚካሄደው ኦዲት በሕጋዊ መንገድ ይከናወናል።

ግዙፍ ተቋሞች እጅ የገባው የካሎቲ ወርቅ

ዲኢኤ የመራው ምርመራ እንደሚጠቁመው፤ ካሎቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ ወጥ ገንዘብ ወደ ሕጋዊ መስመር ያስገባው በነሐሴ 2014 ነው።

በካሎቲ የተሸጠ ወርቅ በግዙፍ ተቋሞች እጅ ገብቷል።

ስዊዘርላንድ የሚገኘው ግዙፍ የወርቅ አምራች ቫልካምቢ ከካሎቲ ወርቅ ከገዙት መካከል ይጠቀሳሉ።

ቫልካምቢ ከ2018 እስከ 2019 ድረስ ወደ 20 ቶን ወርቅ ከካሎቲ ገዝቷል። 60 ቶን ወርቅ ደግሞ ከካሎቲ ጋር ግንኙነት ካለው አካል ሸምቷል።

ከላሎቲ ወርቅ መግዛቱን ግን ማመንም መካድም እንደማይችል ተናግሯል።

ተንቀሳቃሽ ስልኮች (በተለይም ስማርትፎን) ከሚሠሩባቸው ንጥረ ነገሮች አንዱ ወርቅ ነው።

ስልክ አምራቹ አፕልም ከካሎቲ ወርቅ ገዝቷል።

አፕል ባወጣው መግለጫ “ወርቅ አጣሪ ድርጅት ያስቀመጥነውን ደረጃ የማይመጥን ከሆነ ወይም ፍቃደኛ ሆኖ ካልተገኘ ምርቱን መግዛት እናቆማለን። ከ2015 ወዲህ ከ63 ተቋሞች ጋር ስምምነታችንን አፍርሰናል” ብሏል።

አያይዞም “ከ2015 ጀምሮ ገለልተኛ አካል ያደረገው ምርመራ እንደሚያሳየው የካሎቲ ወርቅ በአፕል ምርቶች ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ማስረጃ የለም” ሲል አቋሙን አስታውቋል።

ካሎቲ ለጄነራል ሞተርስ እና ለአማዞንም ወርቅ ማቅረቡን የምርመራ ሰነዶች ያሳያሉ።

መኪናዎች ሲገጣጠሙ ወርቅ የሚጠቀመው ጄነራል ሞተርስ ከካሎቲ ጋር ቀጥታ የንግድ ግንኙነት እንዳልነበረው እና ለምርት የሚያውለውን ቁሳቁስ የሚያቀርቡለትን ተቋሞች ኃላፊነት በተሞላው መንገድ እንደሚመርጥ ገልጿል።

ምርት ከሚያቀርቡለት መካከል ስለ ካሎቲ ቅሬታ ያቀረበለት እንደሌለም አክሏል።

አማዞን በበኩሉ “ምርት የሚያቀርቡልኝ ተቋሞች ሰብአዊ መብትና የአካባቢ ጥበቃ ሕግጋትን የሚያከብሩ መሆናቸውን አረጋግጣለሁ። የምንጠቀምባቸው ንጥረ ነገሮች ከየት እንደሚመጡ በማጣራት ረገድ ምርት አቅራቢዎቻችን እንዲተባበሩን እንጠብቃለን” ብሏል።

ለዓመታት ስለ ካሎቲ ምርመራ ሲያደርጉ የነበሩና ሕገ ወጥ ገንዘብ ወደ ሕጋዊ ማስገባቱን ያጋለጡት አካላት የአሜሪካ ግምዣ ቤት ለጉዳዩ ትኩረት አለመስጠቱ አስቆጥቷቸዋል።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ የማይሹ የዲኢኤ ሠራተኛ፤ “ለሦስት ዓመታት ለፍተናል። ሕይወታችን ምርመራው ሆኗል። ከበቂ በላይ ማስረጃ ነበረን ብለን ስለምናምን ሁላችንም ተበሳጭተናል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።