የዓለም መነጋገርያ የሆኑት አፈትልከው የወጡት ዶሴዎች ይዘት ምንድነው?

አፈትልከው የወጡ ዶሴዎች የዓለማችን ግዙፍ ባንኮች ወንጀለኞች ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲያደርጉ መፍቀዳቸውን አረጋግጠዋል።
2 ትሪሊየን ዶላር ልውውጥ የተመዘገበባቸው የፋይናንስ ሰነዶችም የዓለም መነጋገሪያ ሆነዋል።
እነኚህ የፊንሴን (FinCEN) ዶሴዎች ወደ ምዕራቡ ዓለም ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንዳይችሉ ማዕቀብ ተጥሎባቸው የሚገኙ ግለሰቦች እና ቡድኖች እውቅ ባንኮችን ተጠቅመው ገንዘባቸውን ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር አጋልጠዋል።
ፊንሴን (FinCEN) የአሜሪካ የፋይናንስ ወንጀል ተቆጣጣሪ ኔትዎርክ ሲሆን፤ የፋይናንስ ወንጀሎችን የሚከላከል የአሜሪካ የግምዣ ቤት አካል ነው።
ከአሜሪካ ውጪ ጭምር በአሜሪካ ዶላር የሚደረጉ ግብይቶች ሪፖርት ይቀርቡለታል።
ከ2500 በላይ የሚሆኑትን የፊንሴን ዶሴዎች የባንክ ደንበኞች ሚስጢራዊ የገንዘብ ዝውውሮችን የያዙ ናቸው። ዶሴዎቹ ለበዝፊድ ኒውስ የተላኩ ሲሆን ከዚያም በ88 አገራት ለሚገኙ ለ108 መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ተጋርተዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች ዶሴዎቹን መነሻ በማድረግ ጉዳዩ በጥልቀት በመመርመር ባንኮች ሕዝቡ እንዲያውቅ የማይፈልጉትን እውነታ ይፋ አድርገዋል።
አንድ ሰው ከሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ትርፍ ለማግኘት ካሰበ ቀድሞ መዘጋጀት ያለበት የሚያገኘውን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ መቻል ነው።
ይህ ማለት በሙስና ወይም በእጽ ዝውውር የተገኘን ሕገ-ወጥ ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ በባንክ ማስቀመጥ ማለት ነው።
ባንኮች በበኩላቸው ከደንበኞቻቸው የሚቀበሉት ሕገ-ወጥ ገንዘብ አለመሆኑን የማጣራት ግዴታ አለባቸው።
በአንድ ባንክ ሕገ-ወጥ ገንዘብ ሕጋዊ መስሎ ተቀምጦ ቢገኝ ባንኩ ብዙ ሕጎችን ተላልፎ ይገኛል ማለት ነው።
ባንኮች የደንበኞቻቸውን ማንነት ማወቅ ግድ ይላቸዋል። በስርዓታቸው ውስጥ አጠራጣሪ የገንዘብ እንቅስቃሴ ሲያስተውሉ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሳወቅም ይኖርባቸዋል።
ማሳወቅ ብቻ ግን በቂ አይደለም። የገንዘብ እንቅስቃሴው ሕገ-ወጥ መሆኑን ካረጋገጡ የገንዘብ እንቅስቃሴውን ማገድ ይኖርባቸዋል።
የምርመራ ጋዜጠኞቹ ቡድን አባል የሆኑት ፈርገስ ሼኤል ይፋ የተደረጉት ዶሴዎች “በመላው ዓለም ሕገ-ወጥ ገንዘብ ሲንቀሳቀስ የነበረው በባንኮች እውቅና ነው” ብለዋል።
በሕገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር ነበር የተባለው እና አፈትልከው በወጡት ዶሴዎች ከተረጋገጠው 2 ትሪሊዮን በላይ መሆኑም ተጠቅሷል።
ዶሴዎቹ ምን አጋለጡ?
በዓለማችን በግዙፍነቱ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው እና መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው HSBC (ኤችኤስቢሲ) ባንክ አጭበርባሪዎች የተሰረቀ ገንዘባቸውን በመላው ዓለም እንዲያንቀሳቅሱ ፈቅዷል።
ባንኩ የደንበኞቹ የገንዘብ ምንጭ ከአሜሪካ መንግሥት እየተነገረውም የገንዘብ ዝውውሩ እንዲደረግ ፈቅዷል።
የአሜሪካው JP Morgan (ጄፒ ሞርጋን) ባንክ በተመሳሳይ በአሜሪካው ኤፍቢአይ ከሚፈለጉ ቡድኖች መካከል የአንዱ ቡድን የሆነ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲንቀሳቀስ ፈቅዷል።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን አጋር እንደሆኑ የሚታመኑ ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰብ ባርክሌይስ ባንክን በመጠቀም ገንዘባቸውን በምዕራቡ ዓለም እንዲያንቀሳቅሱ ፈቅዷል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ማዕከላዊ ባንክ ከኢራን ጋር ግነኙነት ያለው ድርጅት ገንዘብ እንዲያንቀሳቅስ መፍቀዱን አረጋግጧል።
የጀርመኑ Deutsche Bank (ዶቼ ባንክ) የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች፣ አሸባሪዎች እና እጽ አዘዋዋሪዎች ሕገ-ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስለው እንዲጠቀሙ ፈቅዷል ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ (Standard Chartered) ሽብርን የሚደግፉ ሰዎች ገንዘባቸውን ጆርዳን ወደሚገኝ ባንክ ለአስርት ዓመታት ሲያስተላልፍ መቆየቱን አረጋግጧል።












