ኮሮናቫይረስ፡ "ከመንግሥት በላይ ለጤናዬ የሚጨነቅ አምላክ ስላለ ጭምብል አላጠልቅም" አሜሪካዊቷ ከመቶ ዓመታት በፊት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከመንግሥት በላይ ለጤናዋ የሚጨነቅ አምላክ ስላለ ወረርሽኙን ለመከላከል ጭምብል እንደማታጠልቅ አንዲት አሜሪካዊት ሴት ተናገረች።
ይህ አባባል የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የወጣውን ጭምብል ማጥለቅ እምቢተኝነት በማሳየት አሜሪካውያን ለተቃውሞ ከመውጣታቸው አንፃር በቅርቡ የተነሳ ይመስላል።
ግን አይደለም ይሄንን የተናገረችው የዴንቨር ነዋሪ ከመቶ ዓመታት በፊት የታላቁ ኢንፍሉዌንዛ፣ ስፓኒሽ ፍሉ ወይም በኢትዮጵያ የኅዳር በሽታ ተብሎ የሚጠራውን ወረርሽኝ ለመከላከል የወጣን መመሪያ በመቃወም ነው።
መቶ ዓመታት ወደፊት እንምጣና በአሁኑ ወቅት በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ ከአርባ ግዛቶች በላይ ተጠቅተዋል።
በየቀኑም አዳዲስ ሞቶችና በወረርሽኙ የሚጠቁ ሰዎችን ታሪክም መስማት የተለመደ ሆኗል። በወረርሽኙ ቀዳሚ በሆነችው አሜሪካ ከአምስት ሚሊዮኖች በላይ ሰዎች ተጠቅተዋል፤ ከ160 ሺዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።
የጤና ባለሙያዎችም በተደጋጋሚ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እርምጃዎችን ተግባራዊ ልታደርግ ይገባል ካለበለዚያ ግን ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ወደ ኋላ መመለስ ይከብዳልም ይላሉ።
የቫይረሱን ስርጭትም ለመቆጣጠር አካላዊ ርቀትን መጠበቅና በሕዝባዊ ቦታዎች ላይ የፊት ጭምብል ማድረግ በአሁኑ ወቅት ዋነኛ መከላከያ መንገዶች ናቸው በሚልም በርካታዎች እየተገበሩት ይገኛሉ።
ምንም እንኳን በርካታ አሜሪካውያን ጭምብል ማድረግን በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ቢቀበሉትም፤ በሕዝባዊ ቦታዎች ላይ ጭምብል አናደርግም የሚል እምቢተኝነት ተንፀባርቋል። የተለያዩ ግዛቶችም እነዚህን መመሪያዎች ማስከበር አዳግቷቸዋል።
በርካታ ሰልፈኞች በስኮትስዴል፣ አሪዞና፣ ኦስቲን፣ ቴክሳስና ሌሎች ከተሞች ግዛቶች ያወጧቸውን ጭምብል የማጥለቅ መመሪያዎችን በመቃወም በከተሞቹ ከንቲባ ፅህፈት ቤቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ተቃዋሚዎች መብታችን እየተገፋ ነው የሚሉ ድምፆች በመበርታታቸውም ዋሽንግተንና ሰሜን ካሮላይና የመሳሰሉ ግዛቶች መመሪያዎቹን ተግባራዊ አናደርግም የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።

እስቲ በታሪክን ወደኋላ እንጓዝና በጎርጎሳውያኑ 1918 የነበረውን ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) ወረርሽኝን እንይ።
ከመቶ ዓመታት በፊት ክትባትም ሆነ መድኃኒትም በሌለበት ሁኔታ የታላቁ ኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ እንዳይዛመት የተለያዩ መመሪያዎች መውጣት ነበረባቸው።
ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት ተዘጉ፤ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ታገዱ፤ በጉንፋኑም የተጠቁት ሰዎች እንዲለዩና ተገልለውም ለብቻቸው እንዲቆዩ ተደረጉ።
የዚህን ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር ዜጎች ጭምብል እንዲያጠልቁ ታዘዙ። ቁጣዎችን የቀሰቀው ለይቶ ማቆያው ሳይሆን ጭምብል አጥልቁ መባሉ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለአገራችሁ ስትሉ እድርጉት
ወቅቱ ጥቅምት አጋማሽ 1918 ነበር፤ በሰሜን ምሥራቅ የአሜሪካ ግዛቶች አሰቃቂ የሚባል ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመሆኑ የመንግሥት የጤና ኃላፊዎች ሁሉም ዜጎች አፍና አፍንጫቸውን በጭምብል እንዲሸፍኑ ጠየቁ።
ቀይ መስቀልም እንዲሁ ዜጎች ጭምብል እንዲያጠልቁና በቀላሉም በቤታቸው ውስጥ ካሉ ጨርቆች፣ ክሮችም ሆነ ፋሻዎች ጭምብል አስራርንም ለማበረታት በጋዜጦች ላይ ማስታወቂያዎችን ያወጣ ነበር።
ካሊፎርኒያ፣ ኡታህና ዋሽንግተንን የመሳሰሉ ግዛት ጤና ማዕከላት ደግሞ የራሳቸው ጅምሮች ነበራቸው።
በመላው አገሪቷም ጭምብል ማጥለቅ የዜግነት ግዴታ መሆኑን የሚያትቱ ፖስተሮች መለጠፍ ጀመሩ።
በተለይም የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በጦርነቱ ወቅት ይለፈፉ የነበሩ ፕሮፓጋንዳዎችም በዚህም ወቅት ማኅበራዊ ኃላፊነትና አርበኝነት ጋር በማያያዝም ቀጠሉ።
የሳንፍራንሲስኮ ከንቲባ ጄምስ ሮልፍም "ለአገር ማሰብ፣ አርበኝነት፣ ራስንና ሌሎችን ለመጠበቅ" ጭምብል ማድረግ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው አሉ።
የኦክላንድ ከንቲባ ጆን ዴቪም እንዲሁ "ምንም እንኳን የተለያዩ እምነቶች ቢኖሩንም አርበኝነትና ሌሎችን ማስቀደም ማለት ዜጎችን መጠበቅ የሚቻለው ጭምብልን ስናደርግ ነው" በማለት መንፈስን የሚያነቃቃ መልዕክታቸውን አስተላለፉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መመሪያዎችን ማፅደቅ ፈታኝ ሲሆን
የጤና ኃላፊዎች የሕዝቡ ባህርይ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ፈታኝ እንደሆነ ተረድተውታል፤ በተለይም ጭምብል ማጥለቅ ምቾት ይነሳናልም በመባሉ ማሳመን ፈታኝ ሆኖ አግኝተውታል።
አርበኝነት፣ አገር፣ ብሔራዊ ኃላፊነት የሚሉ አገራዊ ስሜቶችን ለማነቃቃት የሚተላለፉ መልዕክቶችን ማስተላለፍ ብዙ የሚያስኬዱ አልሆኑም።
ለዚያም ነው የካሊፎርኒያው ባለስልጣን "ሰዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲባል መገደድ አለባቸው" ያሉት።
ቀይ መስቀልም እንዲሁ "ወንድ፣ ሴት፣ ልጅ፣ ማንኛውም ጭምብል የማያጠልቅ አደገኛና ለሰዎች የማያስቡ ናቸው" በማለት ጭምብል የማያጠልቁ ሰዎችን በግልፅ በማውገዝ አስተላለፈ።
በርካታ ግዛቶች በተለይም በአሜሪካ በምዕራብ የሚገኙ ግዛቶች ጭምብል ማጥለቅን አስገዳጅ አድርገውትም ነበር። አንዳንዶች አጠር ላለ ጊዜ እንዲታሰሩ እንዲሁም ከ5 እስከ 200 ዶላርም የገንዘብ ቅጣትም የተቀጡ በርካቶች ናቸው።
ሆኖም መመሪያዎቹ በአወዛጋቢነታቸው ቀጠሉ። ለምሳሌ የሳክራሜንቶ የጤና ዳይሬክተር የከተማዋ ኃላፊዎች መመሪያውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ መጠየቅን ጨምሮ፣ መለማመጥና መማፀን ነበረባቸው።
በሎስ አንጀለስ መመሪያው ሊፀድቅ አልቻለም። በፖርትላንድም ረቂቁ ከፍተኛ ክርክርና ውዝግብም አስነስቷል፤ አንደኛው የከተማዋ ምክር ቤት አባልም "ጨቋኝና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው" ሲሉ ወርፈውታል።
"በምንም ተአምር እንደ ውሻ አያስገድዱኘም" አሉ። እንዳሉትም መመሪያው ሳይሳካ ቀረ።
የኡታህ የጤና ኃላፊዎችም በጭምብል አስፈላጊነት ከተወያዩ በኋላ አላስፈላጊ ነው በማለት ውድቅ አድርገውታል። ለዚህም ምክንያታቸው ዜጎች ሐሰተኛ ደኅንነት ስለሚሰማቸውና ባዶ ተስፋም ስለሚሰጣቸው ከመጠንቀቅ ችላ ይላሉ ብለው ነው።
ወረርሽኙ ሁለተኛ ዙር እንደገና ሲያገረሽም ኦክላንድ ጭምብል ማጥለቅ ላይ ሌላ ክርክር ጀመረች። ከንቲባዋ በሌላ ግዛት ውስጥ ጭምብል ሳያደርጉ ተገኝተው መታሰራቸው በጣም አበሳጭቷቸው የነበረ ሲሆን በኦክላንድም ይህ እንዳይደገም ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ።
ይሄንን ክርክር ሲታዘቡ የቆዩ አንድ ታዋቂ ዶክተር በወቅቱም "በዋሻ ይኖር የነበረ ግለሰብ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎችን ቢያይ እብድ ናቸው ይለናል" ብለዋል።
መመሪያዎችን ተግባራዊ የማድግ ፈተና
ጭምብል የማጥለቅ መመሪያዎች ከላይ ቢታዘዙም ነዋሪዎች ግን ሕጎቹን አናከብርም በማለት መጣሳቸው አልቀረም።
የገበያ መደብሮች ጭምብል ያላጠለቁ ደንበኞችን መልሱ ቢባሉም ከመግባት አላገዷቸውም። ሠራተኞችም ጭምብል አጥልቆ መስራት አይመችም በማለት ቅሬታዎችን ያሰሙ ነበር።
የዴንቨር ነዋሪ የሆነች የሽያጭ ሠራተኛም "አፍንጫዋ እየደነዘዘ" በመሆኑ ጭምብል አላጠልቅም ብላ እምቢተኝነቷን አሳየች።
ሌላኛዋ ደግሞ "ከዴንቨር የጤና ቢሮ በላይ ስለ ደኅንነቷ የሚጨነቅ አምላክ" ስላለ አፏንም ሆነ አፍንጫዋን እንደማትሸፍን ተናገረች።
የወቅቱ ጋዜጦች እንደዘገቡት ምንም እንኳን መመሪያው ቢፀድቅም "ሕዝቡ እምቢተኝነቱን በማሳየት ችላ ብሎታል፤ እንዲያውም ትዕዛዙ ማፌዣና መቀለጃ ሆኗል" ብሏል።
እናም ሕጉ ተሻሽሎ ለባቡርና ለአውቶብስ አሽከርካሪዎች ብቻ ጭምብል እንዲያደርጉ ቢታዘዝም እነሱም የሥራ ማቆም አድማ እናካሂዳለን ማለታቸውን ተከትሎ ከተማዋ ጭምብል የማድረግ መመሪያዋን ልታላላ ተገዳለች።
ዴንቨር የሕዝቡን ደኅንነትና ጤንነት የሚያስጠብቅ መመሪያዎች ሳይኖሯትም ወረርሽኙን ተጋፈጠችው።
በሲያትል ግን የአውቶብስ አሽከርካሪዎች ጭምብል ያላጠለቁ ተጓዦችን አናሳፍርም አሉ።
በተለያዩ ግዛቶች መመሪያውን የሚጥሱ ከመብዛታቸው የተነሳ በኦክላንድ የሚገኙ ባለስልጣናት 300 የቀድሞ ወታደሮችን በበጎ ፈቃደኝነት አሰማርተው ነበር። እነዚህ ወታደሮች ሕግ የሚጥሱ ሰዎችን ስምና አድራሻ በመመዝገብ እንዲቀጡ ለባለስልጣናት ይሰጡ ነበር።
በሳክራሜንቶ ጭምብል የማጥለቅ መመሪያው ሲፀድቅ የፖሊስ ኃላፊው "ወደየጎዳናዎቹ ውጡና ጭምብል ያላደረጉ ሰዎችን ስታዩ ይዛችኋቸው ኑ" ብለው ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ።
በሃያ ደቂቃ ውስጥም ፖሊስ ጣቢያው ጥፋተኛ በተባሉት ሰዎች ከአፍ አስከ ገደፉ ተሞላ።
በሳንፍራንሲስኮም መመሪያውን በመተላለፍ የታሰሩ ዜጎች በዝተው የፖሊስ ኃላፊው እስር ቤቶቹ ሞልተዋል በማለት ለከተማው አስተዳዳሪዎች ማሳሰቢያ ለመስጠት ተገደው ነበር።
ዳኞችና ኃላፊዎችም ከሰዓት እላፊ ውጪ አምሽተው መስራት፣ ቅዳሜና እሁድንም ያለ እረፍት በመስራት መመሪያ የተላለፉ ሰዎች ላይ ብይን ይሰጡ ነበር።
ተቃውሞ
ጭምብል ሳያጠልቁ የተያዙት በርካቶቹ ሳይነቃብን የእለት ሥራችንን እናከናውናለን ያሉ ናቸው።
ሆኖም በሳንፍራንሲስኮ ጭምብል ሳያጠልቁ የሚወጡ ሰዎች ከመበርከታቸው ብዛት የተነሳ ሌላ ዙር ወረርሽኘ ለመከሰቱ መንስኤ ሆነ። የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በጎርጎሳውያኑ ጥር 1919 ጭምብል እንዲደረግ ሌላ ትዕዛዝ ለማውጣት ተገደዱ።
ሕዝቡም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ነፃነትን የሚጋፋና መብትን የሚጥስ ነው በማለት አወገዘው።
በጥር 25/1919 ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የፀረ-ጭምብል ከፍተኛ ተቃውሞን አካሄዱ። በዚህ ተቃውሞ ላይ ከተሳተፉት መካከል ታዋቂ የህክምና ዶክተሮች እንዲሁም የሳንፍራንሲስኮ የጤና ቁጥጥር ቦርድ አባላት ይገኙበታል።
ትናንትናና ዛሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ1918 የነበረውን ጭምብል ውጤታማነት በአሁኑ ወቅት ማወቅ አዳጋች ነው።
ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ጭምብሎች ተሻሽለው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መግታት እንደሚችሉም ማረጋገጥ ተችሏል።
ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሆኖ በቀጠለበት ወቅት አሜሪካውያን የፊት ጭምብል ማድረጋቸው አወዛጋቢነቱ እንደቀጠለ ነው።
ለዚህም ስር የሰደደ የግለሰብ ነፃነት፣ በጭምብሎች አደራረግ ላይ ግልፅ ያለ መልዕክት አለመኖር፣ የአመራር ችግር እንዲሁም ስለ ጭምብሎች የሚወሩ መሰረት የሌላቸው መረጃዎች ምክንያት ናቸው ተብሏል።
በአሁኑ ወቅትም እየተከሰተ ባለው ቀውስ ጭምብል ማድረግ አስገዳጅ ሊሆን በተገባ ነበር። በ1918ቱም 675 ሺህ አሜሪካውያን ህይወታቸውን አጥተዋል፤ አሁንም ህይወታቸውን እያጡ ነው።
ታሪክ ራሱን እየደገመ ይሆን?














