ኮሮናቫይረስ፡ የውጭ አገር ተጓዦች የኮቪድ-19 ምርመራ ለማድረግ ፈተና ሆኖባቸዋል

ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አገራት ድንበሮቻቸውን በጥንቃቄ እየከፈቱ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የአየር በረራ መጀመርን ተከትሎ በወጡ አዳዲስ ደንቦች ምክንያት ተጓዦች ከኮቪድ-19 ተህዋሲ ነጻ መሆናቸውን በምርመራ እንዲያረጋግጡ ይገደዳሉ።

በኢትዮጵያ ይህንን ምርመራ በማድረግ ውጤት ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የሆነውና አብዛኞቹ የውጭ አገር ተጓዦችን የሚያስተናግደው ተቋም የምርመራ ፈላጊዎች ቁጥርና አገልግሎቱ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተገልጋዮች እየተናገሩ ነው።

የአየር በረራ አገልግሎት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ በመቆየቱ ለወራት ሲጠባበቁ የነበሩ ተጓዦች ይህንን ምርመራ ለማድረግ ከባድ ፈተና ሆኖብናል ይላሉ።

ምክንያቱ ደግሞ ምርመራውን የሚያከናውነው ተቋም የወሰደውን ናሙና ውጤት ለማሳወቅ ቢያንስ 48 ሰዓታትን ይፈልጋል።

አገራት ደግሞ ተጓዦች ከመሳፈራቸው በፊት ምርመራ እንዲያደርጉ የሚፈልጉበት የሰዓት ገደብ ከ48 ሰዓት እስከ 96 ሰዓት እንደየአገሩ ይለያያል።

ምርመራውን ከብዙ ጥበቃ በኋላ ባለፈው አርብ ዕለት ማድረግ የቻሉ ተጓዦች ውጤት አልደረሰም በመባላቸው በረራቸውን ለመሰረዝ እንደተገደዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ክሊኒኩ ለተመርማሪዎች ውጤት የሚሰጠው የጉዞው ዕለት ወይም ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በ10 ሰዓት ብቻ ነው።

በዚህም ምክንያት የጉዞ ቀን፣ የሚጓዙበት አገር የምርመራ ደንብና የክሊኒኩ ውጤት መስጫ ዕለት ለማጣጣም ፈታኝ እንደሆነ ተጓዦቹ ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ሰኞ ማለዳ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ምርመራ በሚሰጠው ተቋም ደጃፍ ላይ ተሰልፈው ያገኛቸው ተጓዦች ተቋሙ ስለምርመራው በቂ መረጃ እንዳልሰጣቸው፣ በረራቸውን በተደጋጋሚ ለመሰረዝ እንደተገደዱና ላልተጠበቀ ወጪና መጉላላት እንደተዳረጉ ገልጸዋል።

አገልግሎቱን ፈልገው ወደተቋሙ የሄዱ ሰዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት ምርመራውን የሚያደርገው ላቦራቶሪ ሥራውን የሚያስኬድበት ግልጽ አሰራር እንዳልዘረጋም ተናግረዋል።

አገልግሎት ፈላጊዎች የሚስተናገዱት በቅድሚያ በኢሜይልና በስልክ ከተመዘገቡና የጉዞ ትኬታትና የፓስፖርታቸውን ቅጂ ከሰጡ በኋላ ነው የሚል ማስታወቂያ በክሊኒኩ ደጃፍ ላይ የተለጠፈ ቢሆንም፤ በክሊኒኩ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተጠቀሱት የስልክ መስመሮች ከአገልግሎት ወጪ ናቸው አልያም ተዘግተዋል። የኢሜይል ምላሽም ከክሊኒኩ ማግኘት አልተቻለም።

የቢቢሲ ዘጋቢዎችም ይህንኑ ማረጋገጥ ችለዋል።

የክሊኒኩ ሠራተኞች በበኩላቸው ሰዎች ከተመዘገቡ በኋላ በራሳቸው ምክንያት ሊቀሩ ስለሚችሉ ይህንን የቅድመ ምዝገባ አሰራር ትተን ሰዎች እንደ አመጣጣቸው ማስተናገድ ጀምረናል ይላሉ።

ሰኞ ማለዳ በስፍራው ተሰልፈው ከነበሩ ተጓዦች ቢቢሲ እንደተረዳው አንዳንዶቹ ተገልጋዮች እሑድ ከቀትር ጀምሮ ለረዥም ሰዓት አገልግሎቱን ለማግኘት በዝናብ ተሰልፈው የጠበቁ ቢሆንም "አሁን ደክሞናል ከዚህ በላይ አናስተናግድም" በሚል እንዲበተኑ ተደርገዋል።

ሌሎች ደግሞ ነገ በአዲስ መልክ አንሰለፍም በሚል ቅሬታ በማንሳታቸውና የክሊኒኩን በር አናዘጋም በማለታቸው ስም ዝርዝራቸው ተጽፎ በቀጣይ ቀን ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚስተናገዱ ቃል እንደተገባላቸው ተናግረዋል።

ክሊኒኩ በዚህ መንገድ ተገልጋዮቹን ካሰናበተ በኋላ የተወሰኑ ሰዎችን "አሾልኮ እንዳስገባና አገልግሎት እንደሰጣቸው" በቦታው ነበርኩ ያሉ እማኝ ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙ የመኪና አስተናባሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የችግሩን ስፋት በመረዳት በጠዋት ወረፋ በመያዝ ሰልፋቸውን እስከ 200 ብር እየሸጡ እንደሚገኙ ተገልጋዮች ይናገራሉ።

የምርመራ አገልግሎት ሰጪው ተቋም በርካታ ለምርመራ የሚመጡ ሰዎች በሚስተናገዱበት በአንደኛው ቅርንጫፉ በሁለት ነርሶችና በሁለት ናሙና ሰብሳቢዎች ብቻ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሆነና የሚሰጠው ምርመራው አገልግሎቱን ከሚፈልገው ሰው ጋር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ቢቢሲ ለመታዘብ ችሏል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ሰኞ ማለዳ በስፍራው እንደተመለከተ የአገልግሎት ደረሰኝ ወረቀት ማተሚያ ማሽን ብልሽት ገጥሟል በሚልም ክሊኒኩ ለግማሽ ሰዓት ያህል ሥራውን አቁሞ ነበር።

ክሊኒኩ ምንሊክ ሆስፒታል አካባቢና ቡልጋሪያ ባሉት ቅርንጫፎቹ የምርመራ አገልግሎት ይሰጣል ቢባልም የሌሎች ቅርንጫፎቹ ተገልጋዮች ከሌሎች ቅርንጫፎች ይልቅ ወደ አንደኛው ክሊኒክ በብዛት ሄደው ምርመራ ለማግኘት እየጣሩ ነው።

"ወደ ሌላ ቅርንጫፍ ሄደን እድላችንን እንሞክር ስንላቸውም መልስ አይሰጡንም፣ መረጃ እንኳን ማግኘት ብርቅ ነው" ይላሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተገልጋይ።

ሰኞ በዚህ ቅርንጫፍ ረዣዥም ሰልፎች የነበሩ ሲሆን በምንሊክ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የክሊኒኩ ቅርንጫፍ ግን የተገልጋዩ ቁጥር አነስተኛ ሆኖ ታይቷል።

ክሊኒኩ ተመርማሪዎችን አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ብር ለአገልግሎቱ ካስከፈለ በኋላ ውጤቱን የሚሰጠው ከ48 ሰዓታት በኋላ እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ በሚገኘው ቅርንጫፉ ብቻ ነው።

ጠዋት በረራ ያላቸው ሰዎች ውጤት ስለማይደርስላቸው በብዛት ለድጋሚ የትኬት ማስቀየሪያ ወጪ፣ እንዲሁም ለሌላ አዲስ ምርመራ ወጪ እየተዳረጉ መሆናቸውን ቢቢሲ ካናገራቸው ሰዎች ለመረዳት ችሏል።

ቢቢሲ ምርመራውን ከሚሰጠው የኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪስ ምላሽ ለማግኘት በማስታወቂያ ሰሌዳቸው ላይ ባሰፈሩት የስልክ አድራሻ በተደጋጋሚ ቢደውልም ቁጥሩ ስለማይሰራ መልስ ማግኘት አልቻለም።

ኮሮና
Banner