አሜሪካ፡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ሽጉጥ የመዘዙት ጥንዶች ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካዋ ሴይንት ሉዊስ ነዋሪ የሆኑት ባልና ሚስት የተቃውሞ ድምፅ እያሰሙ በበራቸው ያለፉ ሰልፈኞች ላይ የጦር መሣሪያ ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል ተከሰዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ማርክና ፓትሪሺያ ማክሎስኪ የዘር መድልዎን በመቃወም ድምፅ እያሰሙ በበራቸው በኩል ባለፉ ሰዎች ላይ የጦር መሣሪያዎቻቸውን የመዘዙት።
1.15 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል በተባለለት የተንጣለለ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ጥንዶች የጦር መሣሪያ የመዘዝነው ለደህንነታችን በመስጋታችን ነው ሲሉ ክሳቸውን አስተባብለዋል።
ቢሆንም የሴይንት ሉዊስ ጠበቃዎች የጥንዶቹ ተግባር ሰላማዊውን የተቃውሞ ሰልፍ ወደ አመፅ ሊቀይረው ይችላል ነበር ሲሉ ይሞግታሉ።
'የጦር መሣሪያን በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ያሉ ሰልፈኞች ላይ መምዘዝ ሕጋዊ አይደለም። ሁኔታው ወደ ከፋ አመፅ አለመሸጋገሩ መልካም ነው። ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ተግባር በሴይንት ሉዊስ ከተማኣ ተቀባይነት የለውም' ብለዋል የከተማዋ የመጀመሪያው ጥቁር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኪም ጋርድነር።
'በነፃነት ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ መብትን ማስከበር አለብን። ይህንን መብት የሚጋፋ አላስፈላጊ የሆነ ማስፈራራት ተቀባይነት የለውም' ብለዋል አቃቤ ሕጊቷ።
ጥንዶቹ የጦር መሣሪያን ያለአግባብ ከመጠቀም ባለፈ በአራተኛ ደረጃ ጥቃት መፈፀም ወንጀል ይከሰሳሉ ተብሏል።
የጥንዶቹ ጠበቃ ጆዌል ሽዋርትዝ ክሱን 'ልብ የሚሰብር' ብለውታል። አልፎም ምንም ዓይነት ወንጀል ተፈፅሟል ብለው እንደማያምኑ አሳውቀዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጥንዶች 'በገዛ መኖሪያ ግቢያችን ራሳችንን የመከላከል መብት አለን' ሲሉ ይከራከራሉ።
የሚዙሪ ግዛት አገረ-ገዥ ማይክ ፓርሰን ጥንዶቹ ከተከሰሱና ከተፈረደባቸው የምህረት ኃይላቸውን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
'አንዲትም ደቂቃ እሥር ቤት ያሳልፋሉ ብዬ አላሰብም' ሲሉ የሪፐብሊክ ፓርቲው አባል ለአንድ የራድዮ ጣቢያ ተናግረዋል።
አገረ-ገዥው ሕግ አርቃቂ ሳሉ የሚዙሪ ግዛትን 'ካስትል ዶክትሪን' ከፃፉ መካከል ናቸው። ሕጉ፤ ሰዎች ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ የጦር መሣሪያዎች መጠቀም እንዲችሉ የወጣ ሕግ ነው።
የ63 ዓመቱ ባል አቶ ማክሎስኪ እና የ61 ዓመቷ ሚስቱ ፓትሪሺያ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጦር መሣሪያዎቻቸውን ሲመዙ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙዎች ተጋርተውታል።
ሰልፈኞቹ በጥንዶቹ ቤት በኩል አድርገው ወደ ከተማዋ ከንቲባ ሊዳ ክሩውሰን መኖሪያ ድምፃቸውን ለማሰማት በማቅናት ላይ ነበሩ።
የጥንዶቹ ጠበቃዎች ከሰልፈኞቹ መካከል ሁለት ወይም ሶስት ነጭ ሰልፈኞች ጥንዶቹን አስራርተዋል፤ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሊገቡም አስበው ነበር ሲሉ ይከራከራሉ።
የክሱ መዝገቡ እንደሚያሳየው ጥንዶቹ፤ ከሰልፈኞቹ መካከል በርካታ ሰዎች ማለፍ ክልክል ነው የሚለውን ምልክት በመጣስ ወደ ግቢ ገብተዋል ይላሉ።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ደግሞ የብረቱ በር መጀመሪያም ክፍት ነበር ሲሉ ይከላከላሉ።
ሴይንት ሉዊስ ውስጥ የተካሄደው ሰልፍ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፋሎይድ በነጭ ፖሊስ መገደሉን ተከትሎ በአሜሪካ የተቀጣጠለው ተቃውሞ አካል ነው።
የጦር መሣሪያን ያለአግባብ መጠቀም እስከ አራት ዓመታት ድረስ የእሥር ጊዜ ሊያፈርድ ይችላል።














