ትራምፕ የፌደራል ህግ አስከባሪ አካላትን ወደ ትላልቅ ከተሞች እልካለሁ ሲሉ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፍ እየተካሄደባቸው ወደሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በርካታ የፌደራል ህግ አስከባሪ አካላትን እንደሚልኩ በመግለጽ አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ ሰኞ እለት በርካታ በሊብራል ዲሞክራቶች የሚመሩ ከተሞችን የተቹ ሲሆን፣ ቺካጎ፣ ኒውዮርክን የሚያስተዳድሩ ባለስልጣናትንም ስራቸውን ለመስራት ይፈራሉ ሲሉ ወርፈዋቸዋል።
አክለውም ወደ ኦሪጎን የተላኩ የፀጥታ አካላት በፖርትላንድ ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ ህግና ደንብ በማስከበር ረገድ "ተገቢውን ስራ ሰርተዋል" በማለት አንቆለጳጵሰዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ግን የፌደራል ህግ አስከባሪዎች ሁኔታውን አባብሰውታል ሲሉ ይከስሳሉ።
የግዛቲቱ አስተዳዳሪዎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወታደሮቻቸውን ከፖርትላንድ እንዲያስወጡም ጠይቀዋል።
በዋይት ሐውስ ሰኞ እለት መግለጫ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ህግና ደንብ ማስከበር የሚለውን ሃሳባቸውን ደጋግመው በማንሳት ተናግረዋል።
"ህግ አስከባሪ አካላትን እንልካለን" በማለት ለጋዜጠኞች የተናገሩት ትራምፕ "ይህ በከተሞቹ እንዲሆን አንፈቅድም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኒው ዮርክ፣ ቺካጎ፣ ፊላዴልፊያ፣ ዲትሮይት፣ ባልቲሞር እና ኦክላንድን በመጥቀስም በእነዚህ ከተሞች ስላለው ግጭት ተናግረዋል።
"ይህ በአገራችን እንዲሆን አንፈቅድም፣ ሁሉም የሚመሩት በሊብራል ዲሞክራቶች ነው" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ፌደራል የፀጥታ አስከባሪ አካላት በፖርትላንድ ያላቸው ሚና አጨቃጫቂ ቢሆንም አሞካሽተዋቸዋል። ከተማዋ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በሚኒሶታ ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ በደረሰበት መታነቅ ከሞተ በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደባት ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ተሰማርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንዳንድ የፖሊስ ባልደረቦች የፀጥታ አካላት መሆናቸውን የሚያሳይ የደንብ ልብስም ሆነ መኪናቸውን የሚለይ ማንኛውንም ነገር ሳያደርጉ መንቀሳቀሳቸው በዲሞክራቶችና በአክቲቪስቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቷል።
ባለፉት ሳምንታት በተቃዋሚ ሰልፈኞችና በፀጥታ አስከባሪ አካላት መካከል ግጭቶች የተባባሱ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት እነዚህ የፌደራል ህግ አስከባሪ አካላት ግዛታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ እየጠየቁ ነው።
ትራምፕ ግን የኦሪጎን አገረ ገዢ፣ የፖርትላንድ ከንቲባ፣ እና የሌሎች ግዛቶች ህግ አውጪዎች "አናርኪስቶችን" ይፈሯቸዋል ብለዋል።
"እነዚህን ሰዎች ይፈሯቸዋል" በማለት "ለዚያ ነው ሊረዱን የማይፈልጉት" ሲሉም አክለዋል።
እንዲሁም የፌደራል ፖሊሶች በስፍራው የተገኙት ለሶስት ቀናት ብቻ ቢሆንም በአጭር ቀናት ውስት ጥሩ ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል። " መሪዎቻቸውን በቁጥጥር ስር አውለዋል" አናርኪስቶች ናቸው"
ብለዋል ትራምፕ።















