በተቃውሞ ዜማው አለምን ያስደመመው የ12 አመቱ ታዳጊ ዋርነር ሬከርድስ አስፈረመው

ኪድሮን ብርያንት

የፎቶው ባለመብት, Instagram/ Keedron Bryant

የጆርጅ ፍሎይድን በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ መገደልን ተከትሎ የ12 አመቱ ታዳጊ በአሜሪካ ውስጥ ጥቁር አሜሪካዊ ሆኖ ማደግ የፈጠረበትን ፍራቻ ያዜመበት ሙዚቃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልክተውታል።

የአሜሪካው ትልቁ የሙዚቃ አሳታሚ ዋርነር ሬከርድስም ታዳጊው ኪድሮን ብርያንትን አስፈርሞታል።

'መኖር ብቻ ነው የምፈልገው' (አይ ጀስት ዋና ሊቭ) የተሰኘው ሙዚቃው ጆርጅ ፍሎይድ በሞተ በነገታው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ነው የወጣው።

ጥቁር አሜሪካውያን የባርያ ፍንገላ ስርዓትን ማቆም አስመልክተው በሚያከብሩት ጁንቲንዝም ኩባንያው የታዳጊውን አልበም ለማውጣትም እቅድ ይዟል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያገኘው የሙዚቃው ግጥም የተፃፈው በታዳጊው ኪድሮን እናት ነው።

ግጥሙም ላይ በየትኛውም የእድሜ ደረጃ ላሉ ጥቁር አሜሪካውያን ምን ያህል ስጋት እንዳለባቸው በህፃን አንደበቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ገልጾታል"እኔ ጥቁር ታዳጊ ነኝ። በተቻለኝም መጠን ጥሩ ለመሆንም እሞክራለሁ። ነገር ግን አካባቢዬን ስቃኝ በኔ አይነቱ ላይ የሚሰራውን ሳይ፣ በየቀኑ እንደ እንስሳ እየታደንን ነው። ህዝቦቼ ችግር አንፈልግም" የሚሉ መልዕከቶች ተካትተውበታል።

የ Instagram ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን Instagram ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ Instagram ይዘት መጨረሻ

ከዚህም በተጨማሪ ሙዚቃው በኢንስታግራም ሲወጣም ሶስት ሚሊዮን ሰዎች ወደውታል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ፣ ታዋቂው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ሌብሮን ጄምስ፣ ሙዚቀኛዋ ጃኔት ጃክሰንና ተዋናይቷ ሉፒታ ንያንጎ ለታዳጊው ምስጋናቸውን ችረውታል።

"በጣም ነው የሚያስደስተው ምክንያቱም አምላክ የመረጠኝ ይህንን እንዳደርግ ነው" በማለት ታዳጊው ኪድሮን መናገሩን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

አክሎም " ከእናቴም ጋር አብሬ መስራቴ አስደስቶኛል" ብሏል።

እናቱ ጆኔታ ብርያንት ጆርጅ ፍሎይድ እጁ ተጠፍሮ፣መሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱ ላይ ተንበርክኮበት መገደል ከፍተኛ ሃዘን እንደፈጠረባትም ገልፃለች "በቃላት መግለፅ ከምችለው በላይ ነው ልቤን የሰበረው። ምክንያቱም የታዳጊ ጥቁር እናት ነኝ፤ ባለቤቴ፣ ወንድሞቼ፣ አጎቶቼ፣ የአጎት ልጆች፣ ጓደኞቼ ጥቁር ወንዶች ናቸው። ከነሱ ውስጥ አንዳቸው ሊሆኑ ይችሉ ነበር" ብላለች።