የዲሲ ከንቲባ ወደ ትራምፕ ቤተ-መንግሥት የሚወስደውን 'ብላክ ላይቭስ ማተር' ሲሉ ሰየሙት

ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስትያንን ተከትሎ ወደ ቤተ-መንግሥቱ የሚያቀናውን መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወደ ቤተ-መንግሥቱ የሚያቀናውን መንገድ

የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የሆነችው ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ ወደ ትራምፕ ቤተ-መንግሥት የሚወስደውን መንገድ ብላክ ላይቭስ ማተር [የጥቁሮች ሕይወታ ዋጋ አለው] ሲሉ ሰየሙት።

ዴሞክራቷ ጥቁር አሜሪካዊት ከንቲባ ሚዩሪዬል ባውዘር 'የጥቁር ሕዝቦች ሕይወት ዋጋ አለው' የሚል በቢጫ ቀለም ገዘፍ ብሎ የተፃፈበት ወደ ዋይት ሐውስ የሚያቀና መንገድ መርቀው ከፍተዋል።

ከንቲባዋ ፕሬዝደንት ትራምፕ የፌዴራል ሠራዊት ወታደሮችን ከዋሽንግተን እንዲያስወጡ አዘዋል።

ከንቲባዋ ይህንን ያደረጉት የጥቁር አሜሪካዊው በጆርጅ ፍሎይድን ሞት ምክንያት የተቀጣጠለው ተቃውሞ ዋሽንግተን ዲሲ መድረሱን ተከትሎ ነው።

ዋሽንግተን በተቃውሞ መታመሷን ተከትሎ ፕሬዝደንት ትራምፕ በሺህ የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች ከተማዋን እንዲቆጣጠሯት ማዘዛቸው አይዘነጋም። ፕሬዝደንቱ ሰልፈኞች ከመንገድ ገለል እንዲረጉት ከአንድ ቤተ-ክርስትያን ፊት ለፊት ፎቶ ለመንሳት ነበር።

የፕሬዝደንቱ ድርጊት ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን ከግራም ከቀኝም ትችት እንዲዘንብባቸው ምክንያት ሆኗል።

ዋይት ሐውስ ግድም የሚገኘው ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስትያንን ተከትሎ ወደ ቤተ-መንግሥቱ የሚያቀናውን መንገድ የሰየሙት ከንቲባዋ "እኛ የዋሽንግተን ሰዎች በሰላም ተቃውሟችንን ማሰማት እንሻለን። አልፎም መንገዱ ዜጎች የጭቆና ድምፃቸውን ለመንግሥት የሚያሰሙበት እንዲሆን እንፈልጋለንን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ከንቲባዋ ትችት አላጣቸውም። ብላክ ላይቭስ ማተር ግሎባል ኔትወርክ የተሰኘው የጥቁር አሜሪካውያን መብት ተከራካሪ ቡድን የከንቲባዋ ድርጊት አጀንዳ አፍራሽ ድራማ ነው፤ ዋናውን የፖሊሲ ለውጥ ጥያቄ አያካትትም ሲል ተችቶታል።

ምንም እንኳ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ጥቁር አሜሪካውያን ቁጥራቸው ከነጭ አሜሪካውያን ቢልቅም በከተማዋ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ አለመመጣጠን እንዳለ ይነገራል።

ትራምፕ፤ በትዊትር ግድግዳቸው ላይ ከንቲባዋ የፌዴራል ሠራዊት አባላትን የማያንቀሳቅሱ ከሆነ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ወደ ዲሲ አመጣለሁ ሲል ለጥፈዋል። ወንዶችና ሴቶች ሲሉ እነማንን ማለት እንደፈለጉ ግን በግልፅ አላስቀመጡም።

ከንቲባዋ ባለፈው ሐሙስ ፕሬዝደንቱ የጦር ሠራዊታቸውን ከከተማዋ እንዲያስወጡ የሚያትት ደብዳቤ መፃፋቸው አይዘነጋም። አልፎም አሜሪካ የጣለችው የሰዓት እላፊ ዲሲ ውስጥ እንደማይሰራ አሳውቀዋል። ወታደር አንፈልግም፤ ፖሊስ ሰላማዊ ተቃውሞችን ማስተናገድ ይችላልም ብለዋል።

ዋሽንግተን ፖስት እንደፃፈው ከሆነ ቢያንስ 16 ተቋማት ወታደሮቻቸውን ወደ ዲሲ ልከዋል። ከእነዚህም መካከል የሃገር ውስጥ ፀጥታ፣ ኤፍቢአይ፣ የኢሚግሬሽንና ገቢዎች ድርጅት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ብሔራዊው ዘብ ይገኙበታል።

ዋሽንግተን ዲሲ ግዛት አይደለችም። ከንቲባዋ እንደ ግዛት አስተዳዳሪዎች ያለ ሠራዊት የማስገባትና የማስወጣት ስልጣን የላቸውም። የከተማዋ ብሔራዊ ዘብ ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር ነው።