'ፈር ቀዳጅ' ነው የተባለ አዲስ የኮቪድ-19 ህክምና ግኝት ይፋ ተደረገ

የዩናይትድ ኪንገደም ኩባንያ የከናወነው ክሊኒካል ሙከራ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለማከመው 'ፈረ ቀዳጅ' ነው ተባለ።

የፎቶው ባለመብት, BBC Panorama

የዩናይትድ ኪንግደም ኩባንያ ያከናወነው ክሊኒካል ሙከራ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን ለማከመው 'ፈረ ቀዳጅ' ነው ተባለ።

ኩባንያው ባደረገውም ክሊኒካል ሙከራ መሠረት፤ በኮቪድ-19 ተይዘው በሆስፒታል የሚገኙና የኩባንያው የምርምር ውጤት የሆነውን ህክምና የሚያገኙ ታማሚዎች ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል የመግባት እድላቸውን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል ተብሏል።

መቀመጫውን ሳውዝሃምፕተን ያደረገው የባዮቴክ ኩባንያው ሰይንኤርጄን፤ ባካሄዳው በዚህ ሙከራ ላይ ሰውነታችን ኢንፌክሽን ሲያጋጥመው የሚያመርተውን ኢንተርፌርኖ የተሰኘ ፕሮቲን ተጠቀሟል።

ፕሮቲኑ የሰዎችን የበሽታ መከላከል አቅምን ከፍ ያደርጋል በሚል በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ፕሮቲኑን ወደ ውስጥ እንዲተነፍሱት በማድረግ ፕሮቲኑ ወደ ሳምባቸው እንዲገባ ተደርጓል።

ከክሊኒካል ሙከራው በኋላ የተገኘው ውጤት እንደሚያሳያው፤ በኮቪድ-19 ተይዘው ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ ከተደረጉ ሰዎች 79 በመቶው ቬንቲሌተር [የመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ] እንዳያስፈልጋቸው አደርጓል ተብሏል።

ኩባንያው እንደሚለው ከሆነ አብዛኞቹ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ይህ ህክምና ቢደረግላቸው በህመማቸው ምክያት የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ማከናወን ሳያቋርጡ ከበሽታው ሊያገግሙ ይችላሉ።

ህክምናውን ያገኙ ሰዎች ላይ "እጅግ ከፍተኛ" በሆነ መልኩ የትንፋሽ ማጠር ምልክት ቀንሶ ታይቷል። ኩባንያው ጨምሮ እንዳለው ህክምናውን ያገኙ ታማሚዎች በሆስፒታል የሚኖራቸው ቆይታም ይቀንሳል።

በሆስፒታል ውስጥ በአማካይ 9 ቀናት ይቆዩ የነበሩ ታማሚዎች ህክምና ይህ ህክምና ከተደረገላቸው በኋላ የሚቆዩበት ቀናት ወደ 6 ቀናት ቀንሷል።

ክሊኒካል ሙከራው የተካሄደው በዘጠኝ የዩናይትድ ኪንግደም ሆስፒታሎች ውስጥ በሚገኙ 101 በጎ ፍቃደኞች ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ኩባንያው አገኘሁት ያለው 'ፈር ቀዳጅ' ውጤት በጤና መጽሔቶች ላይ አልታተመም። ቢቢሲ የጥናቱን ሙሉ ውጤት የሚያመላክት መረጃ አልተመለከተም። ኩባንያው ግን ኮሮናቫይረስ የሚስከትለውን ኮቪድ-19 በሽታን ለማከም የምርምር ሥራው አመርቂ ውጤት አስገኝቷል እያለ ነው።

በቀጣይ ምን እንጠብቅ?

የሲይንኤርጂን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሪቻርድ ማርስዲን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኩባንያቸው በቀጣይ ቀናት የምርምር ውጤታቸውን ለሚመለከታቸው የአገሪቱ የጤና ኃላፊዎችና ለዓለም አቀፍ የጤና ተቋማት ያጋራል።

ከዚያም በክሊኒካል ሙከራው የተገኘው ውጤት ለሰው ልጆች ማከሚያነት እንዲውል እንጠይቃለን ብለዋል። ይህ ህክምና ከጤና ተቋማትና ከመንግሥታት እውቅና የሚያገኝ ከሆነ ህክናው ለታማሚዎች በስፍት መሰጠት ይጀምራል።

ኮሮና
Banner