የተባበሩት መንግሥታት መኪና ውስጥ ወሲብ ፈፅመዋል ያላቸውን ሰራተኞቹን ያለ ደመወዝ አገደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለት ሰራተኞቹን ንብረትነቱ በድርጅቱ በሆነ መኪና ውስጥ ወሲብ ፈፅመዋል በሚል ያለ ደመወዝ ከስራ እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላልፏል።
ግለሰቦቹ የተባበሩት መንግሥታት አርማ ባለበት መኪና ውስጥ በእስራኤል ቴልአቪቭ ዋና ጎዳና ላይ ሆነው የሚያሳይ ቪዲዮም ወጥቷል።
በቪዲዮውም ላይ ቀይ ቀሚስ የለበሰች ሴትና አንድ ወንድ ከኋላ ወንበር ላይ ወሲብ ሲፈፅሙ ያሳያል።
ይህ የ18 ሰኮንዶች እርዝማኔ ያለው ቪዲዮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች መጋራቱንም ተከትሎ ድርጅቱ በሰራተኞቹ ላይ ምርመራ አከናውኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ቃለ አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በድርጊቱ "እንደደነገጡና ከልባቸውም እንደተረበሹ" ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ በእስራኤል መቀመጫውን ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት ጦር ታዛቢ አካል የሆነው የሰላም አስከባሪዎች ናቸው ተብሏል።
ሰራተኞቹ ያለ ደመወዝ ከስራ የታገዱት ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስም ነው።
ቃለ አቀባዩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አለም አቀፍ ሰራተኞችን በተመለከተ ሊያሳዩት የሚገባ ባህርይና የተወነጀሉበትም ድርጊት "አፀያፊ ከመሆኑ" አንፃር እገዳው ተገቢ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሲባዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ህግ አለው። ነዚህን ህጎች የጣሱ ሰራተኞች ቅጣት እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ዘመቻዎችም ሊታገዱ ይችላሉ።
ነገር ግን ቅጣትም ሆነ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነቱ ሰላም አስከባሪዎቹ የተሰማሩበት ሃገር ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች እንዲሁም ሌሎች ሰራተኞች በወሲብ ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተወነጀሉ ነው፤ ይህም ሁኔታ በቅርብ አመታት ጨምሯል።
በባለፈው አመት 175 ሰራተኞቹ ወሲባዊ ብዝበዛን በመፈፀም መወንጀላቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ።
ከነዚህም ውስጥ 16ቱ ማስረጃ የተገኘላቸው ሲሆን፣ 15ቱ የማስረጃ ድጋፍ የላቸውም ሌሎቹ ደግሞ በምርመራ ላይ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በድርጅቱ ውስጥ ያልተገቡ ወሲባዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ምንም ምህረትም እንደሌለ አስታውቀዋል።












