አራት የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች እርቃኑን የሆነ ግለሰብ ቤቱ እንዳይገባ በመጎተታቸው ከስራ ታገዱ

እርቃኑን የሆነው ደቡብ አፍሪካዊ

የፎቶው ባለመብት, LudidiVelani/Twitter

በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን የሚገኙ አራት ፖሊሶች አንድን ግለሰብ እርቃኑን ከቤቱ እየጎተቱ ማውጣታቸውን ተከትሎ ከስራ ታግደዋል።

ሲጎትቱም የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ወጥቷል። ግለሰቡ መሬት ላይ ሲጥሉትና ካየልትሻ በተባለውም ሰፈር በሚገኘው ቤቱም ሊገባ ሲል እንዳይገባ በሚልም መጎተቱንም ቪዲዮው ያሳያል።

አምልጧቸው በቆርቆሮ ወደተሰራ ቤቱ ጋር ቢገባም የፊት በሩ በመገንጠሉ በጀርባ በኩል እርቃኑም ተጋልጦ ታይቷል።

የደቡብ አፍሪካ የቤቶች ሚኒስትር ሊንዲዌ ሲሱሉ ክስተቱን "ኢሰብዓዊ" ብለውታል።

"የሰውን ልጅ ክብር እንዲህ ዝቅ የሚያደርግና የሚያዋርድ ተግባርን በፍፁም እናወግዛለን" ያሉት ሚኒስትሯ አክለውም "እንዲህ አይነት አፀያፊ ተግባር በዲሞክራሲያዊቷ ደቡብ አፍሪካ ቦታ የለውም" ብለዋል።

የኬፕታውን ደህንነትና ፀጥታ ኃላፊ ሪቻርድ ቦስማን ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ " በክስተቱ ላይ የተሳተፉት አራት ግለሰቦችን ለማገድ ሂደት ላይ ነን" ያሉት ኃላፊው ምርመራም እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል

"በቪዲዮው ላይ እንደታየው በተፈፀመው ተግባር አዝነናል። እንዲህ የሰውን ክብር በሚያወርድ መልኩ አባላቶቻችን መሳተፋቸውን ዝም ብለን የምናየው አይደለምም" ብለዋል።

የሃገሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ቪዲዮው የተቀረፀበት የካየልትሻ ሰፈር አካባቢ ለልማት በሚል ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላልፏል።

በአካባቢውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቤት መቀመጥ መመሪያ እስኪነሳ ድረስ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው 49 ቤቶች ብቻ መሆናቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

"ህገወጥ የተባሉ ቤቶችም ቢፈርሱም በየቀኑ አዳዲስ እየተገነቡ ነው" በማለት አስረድተዋል።