የተባበሩት መንግሥት 'መኪናዬ ውስጥ ወሲብ የፈጸሙትን' ሰዎች እመረምራለሁ አለ

የተባበሩት መንግሥታት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ንብረት በሆነ መኪና ውስጥ ወሲብ የሚፈጽሙ ሰዎች ምስል ከወጣ ወዲህ ድርጅቱ በድርጊቱ 'እጅግ እንደተናገጠ' አሳውቋል።

በማኅበራዊ ሚድያዎች የተሰራጨው ቪድዮ በእስራኤሏ ቴል አቪቭ ከተማ መሐል መንገድ ላይ በቆመ የተባበሩት መንግሥታት መኪና ውስጥ ወሲብ ሲፈጸም ያሳያል።

የተባበሩት መንግሥታት አርማ ያለባት ነጭ መኪና የኋላ ወንበር ላይ አንዲት ቀይ የለበች ሴትና ወንድ ወሲብ ሲፈፅሙ የተቀረፀውን ምስል በርካቶች ተመልክተውታል።

ድርጅቱ ክስተቱን እመርምራለሁ፤ ድርጊቱን የፈፀሙትን ሰዎችም ማንነት እደርስበታለሁ ብሏል።

ወሲብ ሲፈፅሙ የታዩት ሰዎች እስራኤል ውስጥ ሰላም ለማስከበር የሄዱ የድርጅቱ አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ድርጅቱ አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፋኒ ዱጃሪክ የ18 ሰከንዱን ተንቀሳቃሽ ምስል 'አስፀያፊ' ሲሉ ገልፀውታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወሲባዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ሕግ አለው። እኒህን ሕጎች ጥሰው የተገኙ ሰዎች ከድርጅቱ ሊባረሩ ይችላሉ። ሠራተኞቹን የመክሰስና ሌሎች የቅጣት እርማጃዎችን የመውሰድ ኃላፊነት ግን ግለሰቦቹ የመጡበት አገር ነው።

ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወሲባዊ ጥቃቶች በመፈፀም ብዙ ጊዜ ይወነጃለሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ያሉ የድርጅቱ ሠራተኞች በወሲባዊ ጥቃቶች ሲወቀሱ መስማት የተለመደ ሆኗል።

የጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ምስሉ የተቀፀበት አድራሻ ታውቋል፤ ድርጊቱን የፈፀሙት ሰዎች ማንነትም በቅርቡ ይታወቃል ብለዋል።

ምስሉ ላይ እንደሚታየው ከሆነ አድራሻው ቴል አቪቭ ውስጥ ሃያርኮን የተሰኘ መንገድ ላይ ነው።

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች የሴቶች ክፍል ኃላፊ ሄዘር ባር ድርጅቱ ከዚህ የከፉ ወሲባዊ ትንኮሳ ክሶች አሉበት ይላሉ።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች 175 ወሲባዊ ትንኮሳዎችና ጥቃቶችን የተመለከቱ ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።