የተባበሩት መንግሥታት የማዕከላዊ አፍሪካ የተራድኦ ሥራውን አቋረጠ

የተባበሩት መንግሥታት አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት፤ በማዕከላዊ አፍሪካ ተወክሎ የነበረ ግለሰብ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተፈርዶበት የነበረ መሆኑ በመጋለጡ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን አቋረጠ።

የተባበሩት መንግሥታት ከ'ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ' ጋር በመሆን፤ በ'ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ' (ማዕከላዊ አፍሪካ) የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት የተራድኦ ክፍል እንዳለው፤ የቀድሞው የ'ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ' ወኪል የሆነው የቤልጄም ቄስ ሉክ ዴልፋት፤ ህጻናት ይበዘብዝ እንደነበር ክሶች ቀርበዋል።

አሁን ግለሰቡ ከሥልጣኑ መነሳቱ ተገልጿል። የማዕከላዊ አፍሪካ አመራሮች እንዲሁም የቤልጂየም እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ጉዳዩን እየመረመሩም ይገኛሉ።

በማዕከላዊ አፍሪካ መዲና የሚገኙ አቃቤ ሕግ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ቄሱ ላይ ክስ ተመስርቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የተራድኦ ክፍል (ኦሲኤችኤ)፤ ወሲባዊ ጥቃትና ብዝበዛ አንታገስም ብሏል። ተቋሙ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ የምርመራው ውጤት ይፋ እስኪደረግ እገዳው አይነሳም።

ቄስ ሉክ ዴልፋት፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ በወሲባዊ ትንኮሳ ተከስሰው ተፈርዶባቸው እንደነበር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ለ10 ዓመት ያህል ከህጻናት እና ከታዳጊዎች ጋር ከሚያገናኘው ሥራም ታግዶ ነበር።

ሆኖም ግን በ2013 ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ተልኮ፤ 2015 ላይ በ 'ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ' ተቀጥሯል። 'ዲግኒቲ ፋውንዴሽን' እንዳለው፤ ቄሱ የተመደበው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትን ለመከላከል ባቋቋመችው ቦታ ላይ ነው።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ካጋ ባንዶሮ ለሁለት ዓመት ሠርቷል። ከዛም የ 'ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ' ዋና ጸሀፊ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

'ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ'፤ "በወሲባዊ ትንኮሳ ክሶቹ አዝነናል፤ አስቆጥቶናልም" ብሏል። ልጆችን ከጥቃት የሚጠብቁ ፖሊሲዎቹን ለማሻሻል እንደሚሠራም ገልጿል።