"የእንጀራ አባቴ ሁለት ታዳጊዎችን ገደለ፤ እኔ ግን ገዳዮችን የሚጠቁም ካርታ ሠራሁ"

የፎቶው ባለመብት, Sherele Moody
የሸርሊ ሙዲ የልጅነት ሕይወት በስቃይ የተሞላ ነው። ወላጅ እናቷ ያለ ርህራሔ ስትደበድባት ከቤቷ መጥፋትን አማራጭ ብታደርግም፤ የአውስትራሊያ የደህንነት ኃላፊዎች ወደ እናቷ ዘንድ ይመልሷት ነበር።
እናቷ ስትደበድባት፣ እሷ ስትኮበልል፣ ኃላፊዎች ወደ እናቷ ሲመልሷት፣ ዳግመኛ እናቷ ስትደበድባት ዓመታት ተቆጥረዋል። በሰቆቃ የተሞላ ልጅነት ምን እንደሚመስል ሸርሊ ጠንቅቃ ብታውቅም፤ እጅግ የከፋ ነገር የተከሰተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1990 ነበር።
በወቅቱ የሸርሊ የእንጀራ አባት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊን ጠልፎ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ደፍሮ፣ ታዳጊዋን ገድሏል። ስቴሲ-አን ትሬሲ የተባለችው ታዳጊ አስክሬን የተገኘው በቆሻሻ መጣያ ላስቲክ ውስጥ ነበር።
የሸርሊ የእንጀራ አባት ቤሪ ሀድሎው የዘጠኝ ዓመቷን ታዳጊ ሲገድል የ18 ዓመት ወጣት ነበረች። ሸርሊ በወቅቱ ከእናቷ ቤት ወጥታ ሥራ ይዛ ነበር። ታናሽ እህቷ ኬረን ችግር ውስጥ እንደሆነች ስትነግራት ግን ሸርሊ ሥራውን ትታ ወደ ቤት ለመመለስ ወሰነች።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of The Courier-Mail
"እናቴ ፍርድ ቤት ውስጥ ድጋፍ ስትሰጠው ማየት ያሳዝናል"
የእንጀራ አባቷ ወደ ቤት እየወሰዳት ሳለ፤ አንዲት ታዳጊ እንደጠፋች ነገራት።
"ይህንን ብሎኝ በነጋታው ልጅቷን ይፈልጉ የነበሩ ሰዎችን ማገዝ ጀመረ። በአደጋ ጊዜ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች የሚለብሱትን የደንብ ልብስ አድርጎ ታዳጊዋን የሚያፈላልጉ ሰዎችን ተቀላቀለ።"
ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች የቤታቸውን በር አንኳኩ። የእንጀራ አባቷም በቁጥጥር ሥር ዋለ።
የሸርሊ እናት ሊዮኒ ባለቤቷን ስትደግፍ፤ ሸርሊ ግን እንጀራ አባቷን ተቃውማ ለምስክርነት ቆመች። "እናቴ ፍርድ ቤት ውስጥ ድጋፍ ስትሰጠው ማየት ያሳዝናል" በማለት ወቅቱን ትገልጻለች።
እናቷ እና የእንጀራ አባቷ ምንም እንዳልተፈጠረ የታዳጊዋ የቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ ተገኝተው እንደነበረ ስታስታውስ ጥልቅ ሀዘን ይሰማታል።

የፎቶው ባለመብት, The Tracy family
የሸርሊ የእንጀራ አባት ስቴሲ-አንን ከመግደሉ በፊት የሌላ ህጻን ሕይወትም ቀጥፎ ነበር። ሳንድራ ቤከን የተባለች የአምስት ዓመት ታዳጊ ጠልፎ፣ ደፍሮ፣ ገድሏታል።
ግለሰቡ ይኖር የነበረው በሁለቱ ታዳጊዎች ቤት አቅራቢያ ነበር። የአምስት ዓመቷን ታዳጊ በመግደሉ ከታሠረ በኋላ የእሥር ጊዜውን ሳይጨርስ ተለቅቆ ነበር። ከእሥር በተለቀቀበት ወቅት የዘጠኝ ዓመቷን ታዳጊ ገድሏል።
"ከእሥር መለቀቅ አይገባውም ነበር" ትላለች ሸርሊ።
እናቷ ይህንን ግለሰብ ወደ ቤቷ ማስገባቷን እንዲሁም መደገፏን ስታስብ ነገሩ የበለጠ ያስቆጣታል።
ሸርሊ አሁን 48 ዓመቷ ሲሆን፤ እናቷን ለመጨረሻ ጊዜ ያየቻት የ21 ዓመት ወጣት ሳለች ነበር። የእንጀራ አባቷ እሥር ላይ እያለ ሞቷል።

የፎቶው ባለመብት, The Bacon family
"የስቴሲ-አን ሞት እንደሚዘነጋ ሳስብ ያናድደኛል"
ሸርሊ የእንጀራ አባቷ ከታሠረ በኋላ መልካም ሕይወት ለመምራት እንዳዳገታት ትናገራለች። ሕይወቷ መስመር መያዝ የጀመረው ትምህርቷን ጨርሳ ጋዜጠኛ ስትሆን ነበር።
"ስቴሲ-አንን ሳላስታውሳት አድሬ አላውቅም፤ ስለሞቷ ሳስብ ጥፋተኛነት ይሰማኛል"
የጥፋተኛነት ስሜቷ ወደ ቁጣ ተሸጋገረ። አንዳች ነገር ማድረግ እንደሚገባትም ታስብ ጀመር። በትርፍ ጊዜዋ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ሕይወታቸው ያለፈ ሴቶች እና ህጻናትን መረጃ በመሰብሰብ 'አውስትራሊያን ፌሚሳይድ ኤንድ ቻይልድ ዴዝ ማፕ' መሰረተች።
'አውስትራሊያን ፌሚሳይድ ኤንድ ቻይልድ ዴዝ ማፕ' በጉግል ላይ የሚገኝ ካርታ ነው። ከ1880ዎቹ አንስቶ አውስትራሊያ ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው የሞቱ ህጻናት እና ሴቶችን ያሳያል።
"የስቴሲ-አን ሞት እንደሚዘነጋ ሳስብ ያናድደኛል" ትላለች። ሕይወታቸው የተቀጠፈ ህጻናት እና ሴቶች እንደዋዛ እንዳይረሱ ካርታው እንደሚረዳም ታምናለች።
በአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች የተገደሉ ሴቶች በካርታው ላይ በሮዝ የልብ ምልክት ተወክለዋል። አንድ ሰው እያንዳንዱን የልብ ምልክት በመጫን ስለሴቶቹ ማንነት ማወቅ ይችላል። ስለ ጥቃቱ የተጻፉ ዘገባዎችም ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Sherele Moody
"ሁሉም አገር ወታደሮቹን የሚዘክርበት ቀን አለው። ጥቃት ደርሶባቸው የሞቱ ግን ይረሳሉ። ጥቃት የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማሳየት እፈልጋለሁ። ሴቶችም፣ ወንዶችም እንዲሁም ህጻናትም ጭምር ጥቃት የሚደርስባቸው በወንዶች ነው።"
አውስትራሊያ ውስጥ በአንድ ሳምንት በአማካይ አንድ ሴት በአጋሯ ወይም በቀድሞ የፍቅር ጓደኛዋ ትገደላለች።
ሸርሊ በካርታው የመዘገበችው የመጀመሪያ ታሪክ የስቴሲ-አን ሲሆን እስካሁን የ1,880 ሰዎች ታሪክ አካታለች።

የፎቶው ባለመብት, Sherele Moody
በእናቷ ድብደባ ይደርስባት የነበረው ሸርሊ ካርታውን የሠራችው ከሕይወት ተሞክሮዋ በመነሳት ነው። ካርታው በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ከጀመረቻቸው ንቅናቄዎች አንዱ ነው።
ካርታው በ12 ወር ብቻ 500,000 ጊዜ ታይቷል።
ሸርሊ ንቅናቄውን የምታከናውነው ያለመሰናክል አይደለም። ብዙዎች እንደሚገሏት፣ እንደሚደፍሯት ይዝቱባታል። ከዚህ በፊት ፈረሷ ተገሏል። ውሻዋም ተመርዞ ነበር።
ፖሊሶች ምርመራ እያደረጉ ሲሆን፤ በዋነኛነት የሚጠረጥሩት በአቅራቢያዋ የሚኖሩ ወንዶችን ነው።
"ካርታው ጥቃቱ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ስለሚያሳይ ወንዶቹ ካርታውን ማጥፋት ይፈልጋሉ" ትላለች።
ከዚህ በተቃራኒው ሸርሊ አውስትራሊያ ውስጥ ለከፍተኛ የጋዜጠኞች ሽልማት ታጭታለች። "እውቅና ማግኘት ደስ ይላል" ስትል የተሰማትን ትገልጻለች።












