በጃፓን የሴቶችን መቀመጫ የሚጎነትሉ ወንዶችን ለመከላከል ሥውር ማኅተም ተዘጋጀ

ስውሩ ማሕተም

የፎቶው ባለመብት, SHACHIHATA

ሁነኛ ጸረ-ለከፋ መሣሪያ በጃፓን ተመርቷል። ዋና ዓለማው በአውቶቡስና በባቡር እንዲሁም ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች የሴቶችን ዳሌና መቀመጫ "ቸብ" የሚያደርጉ አጉራ ዘለል ወንዶችን ለመቆጣጠር ነው።

ዲጂታል ሥውር ማኀተሙ የመዳፍ ቅርጽ ያለው ሆኖ የተሠራ ሲሆን ሴቶች ጥቃት አድራሹ ላይ ፈጥነው ምልክት እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል ተብሏል።

ስለዚህ ሌሎች ሰዎች ወይም የሕግ አካላት ጥቃት አድራሹን በቀላሉ በተለደፈበት ማኅተም ምክንያት ዳናውን ተከትለው ነቅሰው ያወጡታል።

ይህንን ሥውር ማኅተም የፈበረከው ኩባንያ ዓላማዬ የሴቶችን ጥቃት መከላከል ነው ብሏል። ሆኖም በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ ወደውታል ማለት አያስደፍርም። "መሣሪያው ተጠቂዋ ላይ ሥራ የሚያበዛ ነው" ይላሉ።

ኩባንያው ግን የፈበረኩት መሣሪያ የሴት ዳሌን ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ «ቸብ» ማድረግ የለመዱ 'ቅሌታሞችን' ለማደን እንዲረዳ ነው ይላል።

ኩባንያው ረቂቅ ማኀተሙን ለመሥራት ያነሳሳው ባለፈው ግንቦት ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በብዛት የታየውን ሁለት ሴት ተማሪዎች ጥቃት አድራሽ የሆነን ግለሰብ በቪዲዮ እየቀረጹ ሲያሳድዱት የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ተከትሎ ነው።

በእንግሊዝና ዌልስ የጾታ ጥቃቶች ላይ የሚሠራ አንድ ቡድን ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ ስለ ረቂቁ ማኀተም በሰጠችው አስተያየት « የሴቶች ጥቃት ላይ ንግድ ነው የተያዘው» ብላለች። በሰዎች ጥቃትና ፍርሃት መነገድ መልካም ነገር አይደለም ስትል አክላለች።

የቶኪዮ ከተማ ዙርያ ፖሊስ ባወጣው አሐዝ በ2017 ብቻ ወደ 3ሺ የሚጠጉ ሴቶች "ወንዶች በባቡር ውስጥ አላስፈላጊ ንክኪ አድርገውብናል" ሲሉ መክሰሳቸውን ተናግረዋል።

ይህ ተላካፊ ወንዶችን የሚያድነው መሣሪያ ለገበያ በቀረበ በግማሽ ሰዓት ውስጥ 500 ቅጂ ተሸጧል። የአንዱ ዋጋ 20 ፓውንድ ይደርሳል።

ከዚህ ቀደም በየባቡር ጣቢያው የሴቶችን መቀመጫ የሚነካኩ ጋጠወጦችን ለመቆጣጠር በርካታ ካሜራዎች ባቡር ውስጥ ጭምር መተከላቸው ይታወሳል። ካሜራውን መሠረት በማድረግም 6ሺህ ወንዶች በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።

የሴቶችን መቀመጫ ከመጎንተልም አልፎ በሞባይል መቅረጽ በጃፓን የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል።

ጃፓን የጾታ እኩልነትን በማስከበር ረገድ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ሰንጠረዥ ከ149 አገራት 110ኛ ደረጃ ነው ያላት።