መቀመጫቸውን ለማስተለቅ የሚታትሩ ሴቶች እየሞቱ ነው

ይህቺ ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ሕመሙ ከ2 ዓመት በኋላም አልጠፋም

በሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች መቀመጫቸውን ሞንዳላ ለማድረግ ሰማይ ይቧጥጣሉ። የብሪታኒያ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ማኅበር እንዳለው ይህ መቀመጫን የማደለብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ገዳይ እየሆነ መጥቷል።

በዚህ ሳምንት ሁለተኛዋ ብሪታናዊት ሴት ይህንኑ "የብራዚል መቀመጫ" በሚል የሚቆላመጠውን አደገኛ የቀዶ ሕክምና በማድረግ ላይ ሳለች ሕይወቷ አልፏል።

ዳሌንና መቀመጫ የማሞናደሉ ተግባር በተለይ በሆሊውድ ሴቶች የተለመደ ነው።

ሆኖም ሌሎች የሆሊውድ ዕውቅ ሴቶችን በማየት ብቻ ደረጃውን ያልጠበቀ የሕክምና ማዕከላትን ይጎበኛሉ።

የብሪታኒያ የቁንጅና ቀዶ ጥገና ማኅበር ያወጣው ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ ከ3ሺህ ሴቶች አንዷ በዚሁ መቀመጫን የማሞናደል የቀዶ ጥገና ሕክምና ምክንያት ሕይወቷን ታጣለች።

ይህ ሕክምና በተለምዶ ቢቢኤል ወይም (Brazilian butt lift (BBL)) በመባል ይታወቃል። ሂደቱም ስብ ካለው ማንኛውም የሰውነት ክፍል ሥጋ ቦጨቅ አድርጎ ወስዶ መቀመጫ ላይ የመለጣጠፍ ሂደት ነው።

ሴቶቹ ለሞት የሚዳረጉት ከሌላ የሰውነት ክፍል ተቦድሶ የሚመጣው የደለበ ሥጋ መቀመጫ ላይ በሚለጠፍበት ጊዜ የደም ዝውውርን ስለሚገታ ነው።

የ23 ዓመቷ የዌልስ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ይህንን የቀዶ ጥገና ሕክምና ካደረገች በኋላ ለከፋ የጤና መስቅልቅል ተጋልጣለች።

"አሁን እኮ በትክክል እንኳ መራመድ ተስኖኛል" ትላለች።

ኪም ካርዳሺያንን የመሰሉ እውቅ ሴቶች ሞንዳላ መቀመጫ በማሰራት ይታወቃሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪም ካርዳሺያንን የመሰሉ እውቅ ሴቶች ሞንዳላ መቀመጫ በማሰራት ይታወቃሉ

ይቺ ወጣት ጨምራ እንደተናገረችው "መጀመርያ አካባቢ መቀመጫዬ እርጥበት ማመንጨት ጀምሮ ነበር። ይህም ልብሴን ያበሰብሰው ጀመረ" ብላለች።

"ሽታ አለው፤ አስቀያሚ ነገር ነው የሆንኩት፤ ገንዘቤን ባልረባ ነገር በተንኩኝ፤ ጤናዬን አጣሁ፤ የተፈጥሮ ሰውነቴን እወደው ነበር" ስትል በውሳኔዋ መጸጸቷን ተናግራለች።

ይህን መቀመጫ የማደለብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማግኘት በአማካይ 13ሺህ ዶላር (358ሺህ ብር ገደማ) ያስፈልጋል። እስከ 20 ቀናት የሆስፒታል አልጋን መያዝም ይጠይቃል።

ስሟን መግለጽ የማትፈልግ ሌላ ሴት ለቢቢሲ እንደተናገረችው ይህንኑ መቀመጫን የማሞንደል ሕልሟን ለማሳካት የሄደቸው ወደ ቱርክ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ "ዋጋው ከእንግሊዝ በጣም ያነሰ ነበር"።

ሐኪሟን ያየችው ግን ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ ማደንዘዣ ከመውሰዷ ከ10 ደቂቃ በፊት ነበር።

መቀመጫን የማደለብ ቀዶ ጥገና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከቀናት በኋላ ኃይለኛ ትኩሳት እንደጀመራትና ነርሶችንና ሐኪሞችን ለማናገር ስትሞክር ቸል እንዳሏት አስታውሳለች። ሕመሙ ግን አሁንም ከሁለት ዓመት በኋላ እየተሰማት እንደሆነ አምናለች።

50 ከመቶ የሚሆኑት መቀመጫ አሞንዳይ ሴቶች ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑና ቀሪዎቹ ደግሞ ሀንጋሪ፣ ቤልጂየምና ስፔንን መዳረሻ እንዳደረጉ ተመልክቷል።

በነዚህ አገራት ርካሽ ቀዶ ጥገናን የሚያደርጉ ሴቶች ከሕክምና በፊት አስገዳጅ ውል እንዲፈርሙ እንደሚደረግና ሕክምናውን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያጥላሉ ከሆነ በስም ማጥፋት ክስ እንደሚጠብቃቸው ይስማማሉ።