ወሲባዊ ጥቃት ፈፅመዋል ተብለው የሚታሙት አጨቃጫቂው የቡድሃ መሪ ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት ተከታዮቻቸው ላይ አድርሰዋል እየተባሉ የሚወቀሱት ሶጊያል ላካር የተሰኙት ቲቤታዊ የቡድሃ እምነት አስተማሪ በ72 ዓመታቸው ሞቱ።
ላካር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መፅሐፍት የቸበቸቡ ሲሆን ከዳላይ ላማ ቀጥሎ ስኬታማው የቡድሃ መሪ ተደርገው ይቆጠራሉ።
ምንም እንኳ እርሣቸው አድርጌያለሁ ብለው አምነው ባያውቁም ተከታዮቻቸው ላይ ወሲባዊ እንዲሁም ሌሎች አካላዊ ጥቃቶች አድርሰዋል እየተባለ በሰፊው ይወቀሳሉ።
በእርሣቸው የሚደገፍ አንድ ቡድን ምርመራ አድርጎ 'እርግጥ ነው አንዳንድ አማኞች አካላዊ ጉዳት ሳይደርስባቸው አልቀረም' የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር።
በግለሰቡ ስም የሚተዳደር አንድ የፌስቡክ ገፅ፤ ላካር ዕለተ ረቡዕ ታይላንድ ውስጥ ማረፋቸውን አስታውቋል፤ የሞታቸው ምክንያት ደግሞ የደም መርጋት ነው ብሏል።
በጎርጎሳውያኑ 1947 ቲቤት ውስጥ የተወለዱት ላካር የ13ኛው ዳላይ ላማ ሶጊያል ሌርባ ሊንግፓ አምሳል ናቸው ተብሎ ይታመናል [የቡድሃ እምነት ተካታዮች ሶጊያል ሌርባ፤ በላካር ስጋ ተገልጦ ነው ብለው ያምናሉ።]
ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ገብተው 'ኮምፓሬቲቭ ሪሊጅን' ያጠኑ ሲሆን ታዋቂው መፅሐፋቸው [The Tibetan Book of Living and Dying] በዓለም ላይ 3 ሚሊዮን ቅጂዎች ተሸጧል።
ነገር ግን ወሲባዊ እና አካላዊ ጥቃት አድርሰውብናል የሚሉ አማኞች በርካቶች ነበሩ።
በጎርጎሳውያኑ 1994 አንዲት ሴት ወሲባዊ እና ስነ-ልቡናዊ ጥቃት አድርሰውብኛል ስትል የ10 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ብትጠይቅም ፍርድ ቤት ክሷን ውድቅ አድርጎታል።
ላካር ሌሎችም በርካታ ክሶች እና ወቀሳዎች አልተለይዋቸውም። ቢሆንም በርካታ ምዕመናን ከማፍራት አልተቆጠቡም።













