ኮሮናቫይረስ፡ በአሜሪካ ቴክሳስ ወረርሽኙ 'ከቁጥጥር ውጪ' እየሆነ ነው ተባለ

አንዲት ሐኪም በሽተኛ እየረዳች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካ ባለፉት ሳምንታት ወረርሽኙ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ እያገረሸ ነው። በተለይም በደቡባዊና በደቡም ምዕራባዊ ግዛቶች ሁኔታው ከፍቷል።

በዚህ ረገድ የቴክሳስ ግዛት ፈተና ውሰጥ የገባች ይመስላል።

የቴክሳስ አገረ ገዢ ግሬግ አቢት "ወረርሽኙ ያልተጠበቀ አደገኛ መስመር እየያዘ ነው" ብለዋል።

ሚስተር አቢት ሲናገሩ ባለፉት ሳምንታት በግዛቲቱ በወረርሽኙ የሚያዘው አማካይ የሰው ብዛት በቀን 2ሺህ ነበር፤ አሁን ከ5ሺህ አልፏል።

አሁን በአሜሪካ በተህዋሲው የተነካካው ሕዝብ 2 ሚሊዮን ተኩል አልፏል።

ተህዋሲው ሕይወታቸውን የቀማቸው ዜጎች ብዛት ደግሞ 125ሺህ ይሆናሉ።

በመላው ዓለም የሟቾች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከዚህ ቁጥር ከፍተኛው አሁንም የአሜሪካዊያን ነው።

የበሽታው በድንገት ማገርሸት በአሜሪካ ትልልቆቹ ግዛቶች ማለትም ካሊፎርኒያና ቴክሳስ እንዲሁም ፍሎሪዳ ላይ በርትቷል። በዚህም የተነሳ እየላላ የነበረውን ቁጥጥራቸው ጠበቅ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።

ነገሮች በዚህ መንገድ ከቀጠሉ እነ ቴክሳስ የሆስፒታል አልጋ እንኳ ለታማሚዎቻቸው ማቅረብ ሊሳናቸው ይችላል።

ትናንትና እሁድ አገረ ግዢው ሚስተር ግሬግ አቢት እንተናገሩት ከሰሞኑ በቴክሳስ በቀን ሆስፒታል የሚወሰደው ሕዝብ ከአምስት ሺህ በላይ እየሆነ ነው። ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ አልጋ እንኳ አይኖረንም ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ቴክሳስ ማንኛውንም የሚያስፈልጋትን እርዳታ ለማቅረብ በፌዴራል መንግሥት በኩል ዝግጁ ነን ብለዋል።

ማይክ ፔንስ "ቴክሳሳዊያን እባካችሁ ጭምብል አጥልቁ፣ ከልምድ እንደተማርነው ጭምብል ማጥለቅ የተህዋሲውን ስርጭት ገታ ያደርገዋል" ሲሉ መክረዋል።

አፈጉባኤ ናንሲ ፕሎሲ ከአገረ ገዢው ግሬግ አቢት ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ይህ ጭምብልን በመላው አሜሪካ ግዴታ የማድረጉ ነገር ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ሆኖም ሊሆን ያልቻለ ነው ብለዋል።

በአሜሪካ አንዳንድ ግዛቶች ጭምብል ግዴታ መሆኑ ተቃውሞ ቀስቅሷል። ለምሳሌ በዚያቸው በቴክሳስ ግዛት ዋና ከተማ ኦስትን ጭምብል ለምን ግዴታ ይሆናል ብለው የተቆጡ ሰልፈኞች ከሌሎች ጋር ተጋጭተዋል።

ትናንት እሁድ ከቴክሳስ ሌላ አሪዞናም በርካታ ሰዎች በተህዋሲው መያዛቸውን አስታውቃለች።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሙቀቱን በመሸሽ ወንዝ ወርደው ነበር። ምናልባት ያ የፈጠረው መነካካት ይሁን ወይም ሌላ ብቻ በቀን አራት ሺህ ገደማ ሰዎች በተህዋሲው ተነክተዋል።

በአሜሪካ ደቡባዊና ምዕራባዊ ግዛቶች የዶናልድ ትራምፕን ማባበያና ግፊት በመስማት ይመስላል ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደባቸውን ማንሳታቸውን ተከትሎ ነው በርካቶች በተህዋሲው ሊያዙ የቻሉት ተብሏል።

ዶናልድ ትራምፕ አሁንም ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲመለሱና ኢኮኖሚውን እንዲያንቀሳቅሱት ይሻሉ።

ትራምፕ ዳግም የመመረጥ ዕድላቸው የሚወሰነው ምጣኔ ሀብቱ ተንቀሳቅሶ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሲመለሱ ብቻ ነው ይላሉ ፖለቲካ አዋቂዎች።

ሆኖም ግዛቶች በራቸውን መከፋፈታቸው ለተህዋሲው ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ በመሆኑ ውሳኔያቸውን ለማጤን ተገደዋል።

በዚህም የቴክሳስ ገዢ ሪፐብሊካኑ ግሬግ አቢት ቡና ቤቶች እንዲዘጉ፣ ምግብ ቤቶች የመቀመጫቸውን 50 ከመቶ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ አዘዋል።

በአሜሪካ እስካሁን በተህዋሲው ተጠቅቷል የሚባለው ሰው ብዛት ሁለት ሚሊዮን ተኩል ነው ቢባልም ትክክለኛ ቁጥሩ 20 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ሲል የአሜሪካ ማዕከላዊ የበሽታዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን መግለጹ ይታወሳል።

ኮሮና
Banner