68 ቀናት ፅኑ ሕሙማን ክፍል የከረመው የኮቪድ-19 ታማሚ አስደናቂ ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, VIETNAMESE GOVERNMENT
«ሌላ አገር ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ሟች ነበርኩ» ይላል ስኮትላንዳዊው ስቴፈን ካሜሮን የሆስፒታል አልጋው ላይ እንዳለ።
የ43 ዓመቱ አውሮፕላን አብራሪ 68 ቀናት በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ በመተንፈሻ መሣሪያ [ቬንቲሌተር] በመታገዝ ከርሟል። እነዚህን ሁሉ ቀናት የነብስ ግቢ፤ ነብስ ውጪ ትግል ሲያደርግ የነበረው ታድያ ተወልዶ ባደገባት ከተማ ሳይሆን ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ባለችው ሆ ቺ ሚን ነው።
የቪዬትናም ዋና ከተማ ሆ ቺ ሚን ግርግር ይበዛታል። ወጪ ገቢው ብዙ ነው፤ ከባለ አንድ እግር ተሽከርካሪ፣ ባለሁት፣ ሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪዎች እየተጋፉ፤ ፉጨታቸውን እያሰሙ የሚተራመሱባት።
ቪዬትናም 95 ሚሊየን ሕዝብ አላት። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ሲንጥ፤ ያልተናጠች እየተባለች ትንቆለጳጰሳለች። ከዚህ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ በወረርሽኙ የተያዙባት ጥቂት መቶ ሰዎች ናቸው።
የሞተስ? ካሉ መልስ ምንም ነው።
ስቴፈን ቪዬትናም ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል የገባ የመጨረሻው ሰው ነው። በአገሬው መገናኛ ብዙሃን አንድ ስም ተሰጥቶታል 'ታካሚ 91' የሚል። መጋቢት ላይ ህመም አጋጥሞት ሆስፒታል ሲገባ በጤና ባለሙያዎች የተሰጠው ሕጋዊ መለያው ነው።
የስቴፈን የመትረፍ ዕድል 10 በመቶ ነበር።
አብዛኛውን ጊዜ ራሱን ስቶ ነበር። ሐኪሞች 'Ecmo' የተባለ በጣም በፅኑ ለታመሙ ህሙማን የሚገጠም ማሽን ገጥመው ሲከታተሉት ነው የከረመው። ማሽኑ ከታካሚው ሰውነት ደም ይወስድና ኦክስጅን ሞልቶ ደሙን መልሶ ወደ ሰውነቱ ይለቀዋል።
ሐኪሞች ስቴፈን ከትንፋሽ ማጠር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም እክሎች ማዳን ነበረባቸው። የደም መርጋት አንዱ ነበር። ኩላሊቱ መሥራት በማቆሙ ምክንያት ዳያሊስስ ማድረግ ነበረባቸው። የሳንባው የመተንፈስ አቅም ወደ 10 በመቶ ወርዶ ነበር።
ስቴፈን ወርሃ ታህሳስ ላይ ነበር ወደ ቬዬትናም ያቀናው። እንደ አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን አብራሪዎች ወደ ምሥራቅ ያቀናው የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ነው። ለቪዬትናም አየር መንገድ የመጀመሪያ በረራውን ለማካሄድ ሁለት ቀናት ሲቀሩት ሆ ቺ ሚን ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች የሚዝናኑባት አንዲት መጠጥ ቤት ጓደኛውን ለማግኘት አቀና። በወቅቱ ቪዬትናም በበሽታው የተያዙባት ሰዎች ቁጥር 50 ነበር።
ነገር ግን በነጋታው ትኩሳት ይሰማው ጀመር። እሱ የነበረበት መጠጥ ቤት የነበሩ 12 ሰዎች ውጤታቸው ሲመጣ ኮቪድ-19 እንዳለባቸው ተነገራቸው። ስቴፈንም እንደዚያው።
ከዚህ በኋላ ነው የአገሪቱ ባለሥልጣናት መጠጥ ቤቱን ዘግተው ሁኔታውን መመርመር የጀመሩት። ከመጠጥ ቤቱና እሱ ከሚኖርበት አፓርትማ ጋር ግንኙነት ያላቸው 4 ሺህ ሰዎች ተለይተው እንዲቆዩ ተደረገ።
የስቴፈን ጤና እየተቃወሰ ሲመጣ 'ቬንቲሌተር' ተገጠመለት። ሌሎችም የፅኑ ሕሙማን ክፍል መግባት የነበረባቸው ሰዎች ገቡ። ነገር ግን ሌሎቹ ታካሚዎች አንድ በአንድ እየዳኑ ሲወጡ ስቴፈን ይብስበት ጀመር።
ስቴፈን ለመትረፉ አንደኛው ምክንያት ሌሎች ሰዎች ተሽሏቸው ወደ ቤት ሲመለሱ እሱ ብቻ በመቅረቱ ሐኪሞች ትኩረታቸውን እሱ ላይ በማድረጋቸው ነው በሚለው ብዙዎች ይስማማሉ።
ስቴፈን ከበርካታ ቀናት ራስን መሳት በኋላ ሰኔ 5 ነቃ። ስቴፈን አጋዥ መተንፈሻ ተገጥሞለት ፅኑ ህሙማን ክፍል ሲገባ በዓለማችን የኮሮናቫይረስ ተያዦች ቁጥር 1 ሚሊዮን ነበር። ስቴፈን ሲነቃ ቁጥሩ 7 ሚሊዮን ደርሷል።
«በጣም ዕድለኛ ነኝ። እግሮቼ ብቻ ሰውነቴን መሸከም አቅቷቸዋል። ለእሱ ደግሞ በቀን ሁለት ጊዜ 'ፊዚዮቴራፒ' እየሰራሁ ነው» ይላል ስቴፈን። «ከክፍል ክፍል በተሽከርካሪ ወንበር ስወሰድ እንዲሁም ማሽን ሲገጠምልኝ ትዝ ይለኛል፤ የተቀረው ነገር ግን ደብዛዛ ነው አላስታውሰውም።»
ስቴፈን ካሜሮን 20 ኪሎግራም ቀንሷል። አልፎም ከፍተኛ የሆነ ድካም አለበት። ካለፈበት ሁኔታ አንፃር ጭንቀት ሊገጥመውም ይችላል።
«አሁን የምፈልገው አገሬ መግባት ነው። ፀጥ ረጭ ያለ ቦታ ናፍቆኛል። እዚህ ሙቀቱ በጣም ከባድ ነው። ቀዝቀዝ ያለ አየር በጣም ናፍቆኛል።»













