ከባሪያ ንግድ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሁለት የእንግሊዝ ግዙፍ ኩባንያዎች ጥቁሮችን ይቅርታ ጠየቁ

ግሪን ኪንግ የቢራ ሙዚየምና ለንደን የሚገኘው የሎይድስ ህንጻ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግሪን ኪንግ የቢራ ሙዚየምና ለንደን የሚገኘው የሎይድስ ህንጻ አካባቢ

ከዘመናት በፊት ከባሪያ ንግድ ጋር የተቆራኘ ታሪክ አላቸው የተባሉ እድሜ ጠገብ ድርጅቶች በባርያ ፍንገላ ስርዓት ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ ምክንያት ይቅርታ ጠየቁ።

ሁለቱ የዩናይትድ ኪንግደም ድርጅቶች "በታሪካችን አፍረናል፤ ይቅርታ አድርጉልን" ያሉት የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ እየተቀጣጠለ የመጣውን ተቃውሞ ተከትሎ ነው።

አንዱ ድርጅት ግሪን ኪንግ ይባላል። በመላው ዓለም በርካታ የአልኮል መጠጦችን የሚያቀርቡ "ቡና ቤቶች" ያሉት በዕድሜ ግዙፍ ኩባንያ ነው።

የተመሰረተው በጎርጎሳውያኑ 1799 ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም እንደርሱ ቢራ የጠመቀ የለም ይባልለታል። ላለፉት 200 ዓመታትም በሥራ ላይ ቆይቷል።

ግሪን ኪንግ በኢንግላንድ፣ በዌልስና በስኮትላንድ ብቻ 2 ሺህ 700 ቅርንጫፎች አሉት።

የዚህ ግዙፍ ድርጅት መሥራቾች ከነበሩት አንዱ ቤንጃሚን ግሪን በካሪቢያን ሰፋፊ እርሻዎችን በባሪያዎች ጉልበት ያሳርስ፣ ያሳጭድ፣ ያስወቃና ያሰበስብ ነበር።

በዚህም የተነሳ ነው የግሪን ኪንግ ኩባንያ "ላለፈው ታሪካችን ይቅር በሉን" ያለው።

የዚህ ቢራ ጠማቂ ኩባንያ መሥራች የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት 1833 የባሪያ ንግድን በሕግ ሲከለክል ያሳድራቸው የነበሩ ባሪያዎቹ ነጻ ስለሚሆኑበት ለሚደርስበት የንግድ ኪሳራ ከመንግሥት ከፍተኛ መጠን ያለው ካሳ ተከፍሎታል።

ለመርከብ ድርጅቶች መድኅን በመስጠት የሚታወቀው ሎይድስ ሌላኛው ይቅርታ የጠየቀ የዩናይትድ ኪንግደም ግዙፍ የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው።

ይህ ኩባንያ ድሮ ባሪያዎችን በአትላንቲክ ውቅያኖስ ያጓጉዙ ለነበሩ መርከቦች የመድን ዋስትና አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ነው።

ሁለቱም ድርጅቶች ይቅርታ ከመጠየቃቸውም በላይ ለጸረ ዘረኝነት እንቅስቃሴ ገንዘብ እንደሚደጉሙ ቃል ገብተዋል።

ሎይድስ የተመሰረተው እንደ አውሮፓዊያኑ በ1688 ሲሆን ከአፍሪካና ከካሪቢያን የተፈነገሉ ባሪያዎችን ለሚያመላልሱ የመርከብ ድርጅቶች መድን ዋስትና በመስጠት በይበልጥ ይታወቃል።

በዓለም ካሉ እውቅ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው ሎይድስ በተለይም በኃይልና በባሕር ትራንስፖርት መድን በመስጠት ዝነኛ ነው።

ይህ ኩባንያ የሰሞኑን ተቃውሞ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ "በታሪካችን ውስጥ የምናፍርበት የታሪክ ሰበዝ አለ። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን በባሪያ ንግድ ላይ በነበረን ሚና እናፍራለን፤ ይህ ለዩናይትድ ኪንግደምም ይሁን ለእኛ አሳፋሪው ጊዜ ነው፡፡ ይቅር እንድትሉን እንፈልጋለን" ብሏል።

የግሪን ኪንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኒክ ማኬንዚ በበኩላቸው የሚከተለውን ብለዋል።

"ይቅር የማይባል ተግባር ነበር። የእኛ ኩባንያ መሥራች ከባሪያ ንግድ ሀብት ሲያጋብስ የኖረ ሰው መሆኑ የሚያኮራን አይደለም። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ደግሞ የባሪያ ንግድ መቅረት የለበትም ሲል ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል። ይህ ሁሉ የታሪካችን አካል እንደሆነ ባንክድም እኛ የአሁኑን እና ወደፊትን የተሻለ በማድረግ ላይ እናተኩራለን።"

የጆርጅ ፍሎይድን በሚኔሶታ ግዛት፣ ሜኒያፖሊስ ከተማ በነጭ ፖሊስ በግፍ መገደል ተከትሎ በተነሳው ዓለም አቀፍ ተቃውሞ በርካታ ታሪካቸው ከባሪያ ንግድ ጋር የተነካካ ኩባንያዎች ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነው።