8.9 ሚሊዮን ብር የተሸጠው ደብዳቤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫን ጎ እና ጎውገን መሸታ ቤት የጎበኙበትን ምሽት ያሰፈሩበት አንድ ደብዳቤ በ210 ሺህ ዩሮ [በብር ሲሰላ 8.9 ሚሊዮን ገደማ] ተሽጧል።
ደብዳቤው አርቲስቶቹ ቪንሰንት ቫን ጎ እና ፖል ጎውገን አንድ መሸታ ቤት ገብተው በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን የጎበኙበትን ምሽት በምስል ከሳች ቃላት ያሰፈሩበት ነው።
ዕለተ ማክሰኞ ፓሪስ በሚገኘው ድሩዎ የጨረታ ማዕከል ደብዳቤው 210 ሺህ ዩሮ አውጥቷል።
ደብዳቤውን የገዛው የቫን ጎ ፋውንዴሽን [እርዳታ ድርጅት] ነው።
አርቲስቶቹ በ1880 ደብዳቤውን የፃፉት ለፈረንሳዊው ጓደኛቸው ሰዓሊ ኤሚል በርናርድ ነው። ጓደኛሞቹ ሕይወት በፈረንይዋ አርለ ከተማ ምን እንደሚመስል ቁልጭ አድርገው አስፍረዋል።
ጎ እና ጎውገን የተሰኙት ሰዓሊዎች ደብዳቤው ላይ 'የጥበብ አብርሆትን እየመራን' ሲሉ ፅፈዋል።
ጓደኛሞቹ ሰዓሊዎች በአርለ ከተማ የጥበብ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። የጓደኝነታቸው መጨረሻ ግን ያማረ አልነበረም። ለስምንት ወራት ያክል አርለ ከኖሩ በኋላ በመካከላቸው በተፈጠረ መቃቃር ጎውገን ከተማዋን ጥሎ መጥፋቱን ታሪክ ያትታል።
ደብዳቤው ቫን ጎ የአእምሮ በሽታ አጋጥሞት ግራ ጆሮውን ቆርጦ ከመጣሉ ሳምንታት በፊት እንደተፃፈ ይነገራል።
ኔዘርላንዳዊው ሰዓሊ በ1882 ራሱን ማጥፋቱ ይታወቃል።
ውዱ ደብዳቤ አምስተርዳም በሚገኘው የቫን ጎ ሙዚዬም እንደሚሰቀልና ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።
ጨረታ ማዕከሉ ቫን ጎ እና ጎውገን ከጊዜያቸው ቀድመው የተፈጠሩ አርቲስቶች ናቸው ሲል ይገልፃቸዋል። ሰዓሊዎቹ የምንሰራው ሥራ ወደፊት በሚመጣው ትውልድ አድናቆት ያገኛል ብለው ያስቡ እንደነበርም ጨምሮ ያትታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደብዳቤው ምን ይላል?
አርቲስቶቹ በታሪካዊው ደብዳቤ ላይ በአርለ ከተማ የነበራቸውን የሌተ-ቀን ውሎ አስፍረዋል። የሎ ሐውስ በተሰኘ ስፍራ አንድ አፓርታማ ተከራይተው በጋራ እየኖሩ በጋራ እየሰሩ ጥበብን እንደቃኙ አስፍረውበታል።
"አንድ የሚያስገርምህ ነገር ደግሞ እንንገርህ። አንድ ምሽት ወደ አንድ መጠጥ ቤት አምርተን በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን ጎበኘን። ከሥራ በኋላ ያንን ቤት ደጋግመን መጎበኝታችን የማይቀር ነው' ሲል ቫን ጎ ባለ አራት ገፁ ደብዳቤ ላይ የመሸታ ቤት ታሪኩን አስፍሯል።
"ይሄን በምፅፍልህ ሰዓት ጎውገን አቡጀዲውን ዘርግቶ በዚያው ምሽት የጎበኘነውን አንድ ካፌ እየሳለ ነው። ይህንን ስዕል እኔም ስየዋለሁ። እሱ ግን መሸታ ቤት ያያቸውን እየጨመረበት ነው። ድንቅ ስዕል እንደሚወጣው አልጠራጠርም።"
ምንም እንኳ ደብዳቤው ለጓደኛቸው በርናርድ የተፃፈ ይሁን እንጂ በሁለቱ ሰዓሊያን መካከል የነበረውን የቃላት ልውውጥንም የሚያስቃኝ ነው፤ በተለይ ደግሞ በጋራ መኖርና መሥራቱ ምን እንደሚመስል ይቃኛል።
ደብዳቤው ላይ ጎ፤ ጎውገንን "ያልተጨማለቀ፤ የዱር እንሰሳ ደመ ነፍስ ያለው ፍጥረት" ሲል ይገልፀዋል።
ደብዳቤው በሚቀጥለው በሚቀጥለው ጥቅምት በአምስተርዳሙ ቫን ጎ ሙዚዬም ለሕዝብ ዕይታ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።












